ኀዳር ፳፫ (ሃያ ሦስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የአዲስ አበባ አዲሱን ካርታ ወይም ማስተር ፕላን ተከትሎ በክልሉ ተማሪዎች እያካሄዱት ያለው ተቃውሞ ቀጥሎ፣ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ተማሪዎች ሲገደሉ፣ በርካቶች ደግሞ ቆስለዋል። የክልሉ መንግስት በተለያዩ አካባቢዎች ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ አድርጓል።
በደቡብ ምእራብ ሸዋ ቶሌ ወረዳ ባንቱ ከተማ ተማሪዎች ባስነሱት ተቃውሞ አንድ ደጀኔ ሰርቤሳ የተባለ 10ኛ ክፍል ወጣት ተማሪ የተገደለ ሲሆን፣ በምእራብ ወለጋ ጉሊሶ ከተማ በነበረው ተቃውሞ ቆስሎ የነበረ ጫላ የተባለ ተማሪ ህይወቱ ማለፉን የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡
በቡራዩ ከተማ የተነሳውን ተቃውሞ ለማብረድ ደግሞ የጸጥታ ሃይሎች የወረዳውን የካቢኔ አባላት ሳይቀር መደብደባቸው ተሰምቷል። በቡሌ ሆራ ከተማ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ደግሞ ተማሪዎች እነሱን ለማነጋገር የሄዱትን የወረዳውን ከንቲባና ሌሎችንም አመራሮች በድንጋይ ደብድበው አባረዋቸዋል። ተቃውሞው ወደ መሰናዶ ትምህርት ቤቶች የተሸጋገረ ሲሆን፣ የጸጥታ ሃይሎች እርምጃ በመውሰዳቸው ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ ተደርጓል።
በሃረር የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችም እንዲሁ ተቃውሞ አሰምተዋል። በድሬዳዋ ዩኒቨርስቲም ከፍተኛ ውጥረት የነገሰ ሲሆን፣ የታሰሩ ተማሪዎች እንዳሉ መረጃዎችዎች ያመለከታሉ።
መንግስት በእስካሁኑ ተቃውሞ 3 ተማሪዎች ተገድለዋል ብሎአል። የተነሳውን ተቃውሞ ለመቆጣጠር መቻሉንም ገልጿል። ይሁን እንጅ ከየአካባቢው የሚደርሱት መረጃዎች ተቃውሞዎች መቀጠላቸውን የሚያመለክቱ ናቸው።