ከምርጫው በሁዋላ መንግስት “የበቀል ጅራፉን” እያሳረፈብን ነው ሲሉ የደቡብ ክልል የተቃዋሚ አባላት ተናገሩ

ሰኔ ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ምርጫው በአሳፋሪ ሁኔታ መጠናቀቁን ተከትሎ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች የመድረክ ደጋፊዎችን ቤቶች መቃጠላቸውን፣ መደብደባቸውንና ማሳደዳቸውን የአርባምንጭ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
በተለይ በላካ ቀበሌ ብዙ ሰዎች አካላ ጎደሎ ሆነዋል፣ ቤቶቻቸውም ተቃጥሎባቸዋል የሚሉት ነዋሪዎች፣ የቀበሌ አመራሮች ከሰኔ 15 በሁዋላ መግቢያችሁን ፈልጉ እየተባሉ መሆኑን ገልጸዋል። አቶ ዳዊት ጉበዜ እና አዛውንት እናቱ
ወ/ሮ ሃማሜ ሃይሉ ክፉኛ ተደብድበው ሆስፒታል ተኝተዋል። የሁለቱም ሰዎች ቤት በቃጠሎ ሙሉ በሙሉ ወድሟል።
በተለያዩ የአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ የገጠር ቀበሌዎች ፣ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት የድረሱልን ጥሪ እያሰሙ መሆኑንም ነዋሪዎች ገልጸዋል።
በቁጫ ወረዳ ደግሞ ዶላ፣ ጫላ፣ ውበቴ፣ ወያና ዳሆ ቀበሌዎች በታዛቢነት የተሳተፉ ነዋሪዎች የእርሻ መሬታቸውን ተቀምተዋል። ብዙዎችም እየተሰደዱ ወደ ከተሞች እየተሰደዱ ነው።