በግል የጤና ተቋማት ላይ ትችት ቀረበ

ሰኔ ፲፪ (አስራ ሁለት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የማህበራዊ ጥናት መድረክ በቅርቡ ባካሄደው ጥናት በአዲስአበባ የግሉ የጤና ዘርፍ ከፍተኛ የጥራት መጓደልን ይዞ የተጋነነ የአገልግሎት ክፍያ እየጠየቀ መሆኑን ገልጿል።
ጥናቱ በአዲስአበባ ከሚገኙ ክሊኒኮችና ሆስፒታሎች መካከል በ34ቱ ላይ ያተኮረ ሲሆን አገልግሎት ክፍያ (ዋጋን) በተመለከተ በመንግስት ሆስፒታሎች የካርድ ክፍያ አማካይ ዋጋ 5 ብር ሲሆን፣ በግል ክሊኒኮች አማካይ ዋጋ 100 ብር ነው፡፡ የመደበኛ ወሊድ አገልግሎት በመንግስት ሆስፒታሎች በ50 ብር የሚሰጥ ሲሆን በግል ግን በአማካይ 1 ሺ 940 ብር ይጠየቃል፡፡ የትርፍ አንጀት ቀላል ቀዶ ጥገና ለማድረግ በመንግስት ሆስፒታሎች የሚጠየቀው ዋጋ 120 ብር ሲሆን በግል እስከ 2ሺ850 ብር ይደርሳል፡፡
ጥናቱ በአገልግሎት አሰጣጥ ዋጋ ረገድ በመንግሰትና በግል ሆስፒታሎች ያለው ልዩነት በእጅጉ ሰፊና የማይመጣጠኝ መሆኑን አመልክቷል፡፡
ከአጠቃላይ ታካሚዎች 42 በመቶ ገደማ በግል ሆስፒታሎችና ክሊኒኮች መታከም የሚመርጡ ሲሆን፣ ለዚህ ዋናው ምክንያት በፈገሉት ሰዓትና ጊዜ፣ የፈለጉትን ሐኪም መርጠው ማግኘት በመቻላቸው እንዲሁም በንጽህና ረገድ ከመንግስት ሆስፒታሎች ይልቅ የግሎቹ በመሻላቸው መሆኑ ተመልክቷል፡፡
ጥናቱ የጤና ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ በተመለከተ አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ካርድ በመስጠት ደረጃ ለመስጠት የተሞከረ ሲሆን በጥናቱ ከተካተቱት ውስጥ አብዛኛዎቹ የግል ጤና ተቋማት የቀይ ካርድ ሰለባ ሆነዋል፡፡ አንድ የጤና ተቋም ብቻ መስፈርቱን በማሟላት ያለፈ መሆኑን ጥናቱ ጠቁሞ፣ ይህ ደግሞ የጤና አግልግሎት አሰጣት በከፍተኛ የጥራት ችግር ውስጥ መሆኑን ያመለክታል ብሏል፡፡