ከምርጫው ጋር በተያያዘ በምስራቅ ጎጃም የደህንነት ሃላፊ ሆኖ የተሾመው የህወሃት አባል ነው ተባለ

ሰኔ ፲፪ (አስራ ሁለት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በክረምቱ ወቅት 119 የሚሆኑ የብአዴን አባላት በድሬዳዋ ከተማ የደህንነት እና መረጃ መሰብሰብ ስልጠና ተሰጥቷቸው በክልሉ ከተሰማሩት መካካል አንዱ የሆነው ሰራተኛው እንደገለጸው፣ ማንኛውም ደህህነት ሰራተኛ የስለላ ሪፖርቱን ተክሌ ለተባለ የደህንነት ሰራተኛ ሲያቀርብ መቆየቱን ለኢሳት ተናግሯል።
ስልጠናውን ከወሰዱት የደህንነት ስራተኞች መካከል አንዳንዶች በምስራቅ ጎጃም ደብረማርቆስ ከተማ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ሆነው በመመዝገብ መረጃዎችን ሲያስተላልፉ፣ በምርጫ ታዛቢነት እና በተለያዩ ስራዎች ተመድበው ሲሰሩ መቆየታቸውን የሚገልጸው የደህንነት ስራተኛው፣ በአካባቢው ከምርጫው ጋር በተያያዘ ማንኛውንም ስራ ሲያስተባብርና ሲመራ የነበረው ተክሌ በሞሆኑ ፣ የሰማያዊ ፓርቲ አባሉ ወጣት ሳሙኤል አወቀ ግድያ በእርሱ ትእዛዝ የተፈጸመ ነው ሲል ተናግሯል።
ሳሙኤል የምርጫው ውጤት ይፋ በሚሆንበት ጊዜ የምስራቅ ጎጃምን ህዝብ በማስተባባር ተቃውሞ ያስነሳል በሚል ምክንያት ልዩ ክትትል ሲደረግበት መቆየቱን የደህንነት ሰራተኛው ተናግሯል።
ከምርጫ 97 በሁዋላ የምስራቅ ጎጃም ህዝብ የኢህአዴግ የበቀል እርምጃ ካረፈባቸው አካባቢዎች መካከል ዋናው ነው የሚለው የደህንነት ስራተኛው፣ በርካታ የብአዴን የስለላ አባላት ተሰማርተው የህዝቡን እንቅስቃሴ ሲከታተሉ ነበር ብሎአል።
ሳሙኤል በህዝቡ ውስጥ ከፍተኛ ተቀባይነት እንዳለው ለማሳየት ምርጫው ተጭበርበሮ እንኳን ያገኘው ውጤት አመላካች መሆኑን የገለጸው ስራተኛው፣ ከዚህ ቀደም የተደረጉት ድብደባዎችም ሆነ በስልክ በተደጋጋሚ ይነገሩት የነበሩት
መስፈራሪያዎች በተክሌ ትእዛዝ መፈጸማቸውን ተናግሯል።
ድርጊቱ ከተፈጸመ በሁዋላ የብአዴን አዲስ ምልምል ሰላዮች መረጃውን ሊያወጡ ይችላሉ በሚል ፍርሃት ተጠርተው ምንም አይነት መረጃ እንዳያወጡ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸውም ተናግሯል።
የደብረማርቆስ ፖሊስ ስሙ ያልተጠቀሰ አንድ ተጠርጣሪ ግለሰብ በቁጥጥር ስር ማዋሉን ቢናገርም፣ ምንጮች ግን ድራማ ነው ይላሉ። ድርጊቱ ከመፈጸሙ ትንሽ ቀደም ብሎ መብራት እንዲጠፋ መደረጉና ግድያው ከተፈጸመ በሁዋላ ወዲያውኑ
መብራት መምጣቱ ድርጊቱ ሆን ተብሎ መፈጸሙን ጓደኛው አዲሱ ጌታነህ ለኢሳት መግለጹ ይታወሳል። ሰማያዊ ፓርቲ ድርጊቱ በመንግስት በመፈጸሙ ይጣራ ብሎ እንደማይጠይቅ አስታውቋል።
ኢሳት ከአማራ ክልል የደህንነት ስራተኛ የደረሰውን መረጃ በማስመልከት የምስራቅ ጎጃምንና የክልሉን ፖሊስ ጽ/ቤት ለማነጋገር ሙከራ ቢያደርግም አልተሳካለትም።