ፍርድ ቤት አቶ ማሙሸት አማረን ይፈቱ ቢልም ፖሊስ ግን አለቅም አለ

ሰኔ ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በምርጫ ቦርድ የታገደው የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ( መኢአድ ) ፕሬዝደንት የሆኑት አቶ ማሙሸት አማረ ከሳምንታት እስር በሁዋላ በ5 ሺ ብር ዋስ እንዲፈቱ ፍርድ ቤት
ውሳኔ ቢያስተላልፍም፣ ውሳኔው ለሁለተኛ ጊዜ በፓሊስ ተጥሶ ወደ እስር ቤት ተወስደዋል።
ግንቦት 26/2007 ቦሌ የሚገኘው ችሎት አቶ ማሙሸት የቀረበባቸው ክስ እንደማያስከስሳቸው በመግለጽ እንዲፈቱ ቢወስንም፣ ፖሊስ በራሱ ስልጣን አስሮ ተጨማሪ የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ካስጠየቀ በሁዋላ፣ እንደገና ሰኔ 10 ቀን 2007 ዓም
አራዳ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት አቅርቦታል። ፍርድ ቤቱ በ5 ሺ ብር ዋስ እንዲለቀቅ ውሳኔ ቢያስተላልፍም፣ ፖሊስ ግን ይግባኝ እጠይቃለሁ በማለት በስልጣኑ አስሮታል።
የአዲስ አበባ ህዝብ በሊቢያ በአይ ሲ ስ ታጣቂዎች የተገደሉ ኢትዮጵያውያንን ለመዘከር በወጣበት ወቅት፣ የተፈጠረውን ረብሻ አነሳስተሃል በሚል ክስ ቢመሰረትበትም፣ አቶ ማሙሸት ግን በተባለው ቀን ከምርጫ ቦርድ ጋር በነበረው ክስ ፍርድ
ቤት እንደነበር የፍርድ ቤት ማስረጃ ወረቀት በማቅረብ ተከራክሯል። አቶ ማሙሸት ያቀረበው ማስረጃ የማያፈናፍን ሆኖ በመገኘቱ ፍርድ ቤት አቶ ማሙሸት እንዲፈታ ቢወስንም፣ ፖሊስ ቀኑን በአንድ ቀን አሻሽሎ በማቅረብ ይግባኝ ብሏል።
ይግባኝ ከተባለም በሁዋላ የአራዳ ችሎት በዋስ እንዲለቀቅ ቢወስንም፣ ፖሊስ እንደገና ይግባኝ እጠይቃለሁ በማለት ግለሰቡን እያሰቃየው ነው።
አቶ ማሙሸት ከፕ/ር አስራት ወ/የስ ጋር በተያያዘ ለ8 አመታት ታስሮ ተፈቷል። በምርጫ 97 ወቅትም እንዲሁ ለ2 አመታት ያክል ታስሯል። አቶ ማሙሸት በመኢአድ ውስጥ በተፈጠረ ውዝግብ ከመኢአድ አመራር እንዲለቅ ተደርጎ ነበር።
ዘግይቶ ደግሞ ድርጅቱን እንዲመራ ቢሾምም፣ ከቀድሞው የመኢአድ አመራር ጋር በተፈጠረ ውዝግብ በምርጫ ቦርድ ትእዛዝ ከድርጅቱ እንዲባረር ተደርጓል። አቶ ማሙሸት መኢአድን የሚመራው አካል ህገወጥ ነው በማለት በምርጫ ቦርድ ላይ
ክስ መስርቶ በመከራከር ላይ ይገኛል።
በሌላ በኩል ደግሞ የመኢአድ ምክትል ፕሬዝዳንት የሆነው ዘመነ ምህረት፣ መለሰ መንገሻ እና ጌትነት ደርሶ እንዲሁም ም/ል መቶ አለቃ አንተነህ የተባለ ወጣት ከፍተኛው ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበዋል።
ፍርድ ቤቱ ጠበቃ ለማቆም የፈለገ ማን ነው ብሎ ሲጠይቅ ፣ አቶ ጌትነት ደርሶ፣ ” ጠበቃ አልፈልግም ፣ በትዕዛዝ ፍርድ ከሚሰጥ ፍርድ ቤት ምን አገኛለሁ ብየ ጠበቃ አቆማለሁ፣ አላደርገውም፣ የደረሰብኝን በደል መስማት የማይፈልግ ፍርድ
ቤት 2ወር ከ14 ቀን በጨለማ ክፍል መሰቃየቴን እንዳልናገር የሚከለክል ፍርድ ቤት፣ ምን ሊጠቅመኝ ጠበቃ አቆማለሁ፣ በአካሌ ላይ የደረሰውን ጉዳት ለችሎት እንዳላሳይ የሚከለክል ፍርድ ቤት ፣ጠበቃ አያስፈልግም፣ በደረሰብኝ ድብደባ ጆሮየ አይሰማም፣ ብዙ ቦታ ተጎድቻለሁ ህክምና ብጠይቅ የክሴን ሁኔታ አይተው በሽብር የተከሰሰ ህክምና አያገኝም ተብየ ይህንን በደል መስማት የማይፈልግ ፍርድ ቤት” እያለ ሲናገር ዳኛው ማስቆማቸውን የፓርቲው ህዝብ ግንኙነት ም/ል ሃላፊ አቶ
ለገሰ ወልደሃና ገልጿል፡፡
ዘመነ ምህረት በበኩሉ ” ጌትነት በድብደባ ብዛት ጆሮው አይሰማም ጮክ ብላችሁ ንገሩት” ያለ ሲሆን፣ “እኛ በብሄራችን የተነሳ እራቁታችንን ተደብድበናል፣ አሁን ባለሁበት ቅሊንጦ የአገአዚ አባል አንተን እንገድልሀለን እያለ ይዝትብኛል፣
ለህይወቴ እሰጋለሁ ” ለማረሚያ ቤቱ ትእዛዝ ይሰጥልኝ ብሎአል። ፍርድ ቤቱ ንግግሩን እንዲያቆም፣ ባያቆም ችሎት በመዳፈር እንደሚቃጣው አስጠንቅቆታል።
መለሰ መንገሻ በበኩሉ፣ ከመቶ አመታት በፊት የነበሩ የኢትዮጵያ ነገስታት ስም እየተጠራ “ያድኑህ ተብያለሁ፣ ፂሜን በእሳት አቃጥለውኛል፣ እራቁቴን ተደብድቤለሁ” ያለ ሲሆን ሶስቱም ዳኞች ባንድ ጊዜ ተቆጥተው አስቁመውታል።
ችሎቱም ለሀምሌ 16/2007 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቶ ተነስቷል ፡፡