ወጣት ሳሙኤል አወቀ በመንግስት ታጣቂዎች መገደሉን ሰማያዊ ፓርቲ አስታወቀ

ሰኔ ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ፓርቲው ” የሰማዕታት ደም ይጮሃል፤ ይጣራል” በሚል ርእስ ባወጣው መግለጫ ፣ ወንጀሉን የፈጸሙት የመንግስት አካላት ናቸው ብሎአል። ወንጀለኞች ለፍርድ ይቅረቡ ብሎ
እንደማይጠይቅም አስታውቋል።
“ሰኔ 8 ቀን 2007 ዓ.ም በደብረ ማርቆስ ከተማ እጅግ በሚሰቀጥጥ ጭካኔ እንደ እባብ ተቀጥቅጦ የተገደላው የሰማያዊ ፓርቲ ቆራጥ ታጋይ ሳሙኤል አወቀ የስርዓቱ አገልጋዩች ለዓመታት ሲያስፈራሩት፣ ሲደበድቡት፣ ሰርቶ የመኖር መብቱን ሲጋፉት፣ ያልተሳከ የመግደል ሙከራ በተደጋጋሚ ጊዜ ሲፈፅሙበት መቆየታቸውን የሚያረጋግጡ በርካታ ማስረጃዎች ” መኖራቸውንም ፓርቲው አስታውሷል።
“በሰላማዊ ትግል ፅኑዕ እምነት የነበረው ሳሙኤል አወቀ ይደርስበት የነበረውን ለቁጥርና ለዓይነት አታካች የሆነ በደል ተቋቁሞ፣ ትግሉን እንዲያቆም ወይም የሚወዳትን ሕይወቱን አሳልፎ የሰጠላትን ሐገሩን ለቆ እንዲሰደድ ይህ ካልሆነ ግን የእሱን
ሕይወት ለማጥፋት እጅግ ቀላል መሆኑን የስርዓቱ ባለስልጣናት እና ካድሬዎች ደጋግመው ቢነግሩትም በጭቆና ስር ለሚማቅቀው የኢትዮጵያ ሕዝብ የገባውን ቃል ከማጠፍ ይልቅ ሕይወቱን ለመሰዋት እንደሚቀለው የገባውን ቃል በተግባር አስመስክሮ አልፏል፡፡” ሲል ሟቹ ታጋይ ወጣት ሳሙኤል የነበረውን ጽናት አወድሷል።
በማሰርና በመደብደብ አላማውን እንደማያስቀይሩት፤ ከገደሉት ግን ቀሪ ታጋዮች በተለይም የእድሜ አቻዎቹ የሆኑ የእርሱ ትውልድ የሚሰዋለትን ዓላማ ከግብ እንዲያደርሱ “ትግሌን አደራ!! አደራ!!” በማለት ተማፅኖ አስቀምጧል፡፡
እኛም እንላለን፡፡ አደራህ ከባድ ነው፡፡ ቃልህን እናከብራለን፡፡ አላማህንም እናሳካለን!!!!
ሰማያዊ ፓርቲ ” እስከ መቼ በግፍ እንገደላለን?!! ሸፍጠኞችስ እስከ መቼ ይዘባበቱብናል?!! ትግል ለውጤት የሚበቃው በተወሰኑ ቡድኖች ወይም ግለሰቦች መፍጨርጨር ብቻ ባለመሆኑ የግፍ ስርዓት እንዲያበቃ ሁላችንም የሚገባንን የዜግነት ድርሻ ” እንወጣ ሲል ጥሪ አቅርቧል።
መንግስት የሳሙኤልን ግድያ ከግል ጸብ ጋር አያይዞ መግለጫ መስጠቱ ይታወቃል።
ሳሜአል ከመገደሉ በፊት፣ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች እየዛቱበት መሆኑን እና እኔ ብሞት የነጻነት ትግሉን ቀጥሉ የሚል የአደራ መልእክት በፌስ ቡክ ገጹ ላይ አስፍሮ ነበር።