በሰሜን ጎንደር የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ሹፌሮች ያደረጉትን የስራ ማቆም አድማ ተከትሎ የመንግስት ባለስልጣናት እገዳ ጣሉ

ሰኔ ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በተለያዩ ሰበብ አስባቦች የሚጣልብን ቅጣትና እገዳ ተገቢ አይደለም በሚል ሰኔ 8፣ 2007 ዓም ለአንድ ቀን የስራ ማቆም አድማ አድርገው የነበሩት የሰሜን ጎንደር ዞን ሾፌሮች፣ ፣ ከአድማው በሁዋላ ችግራቸውን የሚሰማ እና መፍትሄ የሚሰጥ አካል ይኖራል ብለው ሲጠብቁ፣ በተቃራኒው ከስራ መታገዳቸውን ተናግረዋል።
ሾፌሮች እና ባለሃብቶች እንደሚናገሩት “የመንግስትን ትእዛዝ አላከበራችሁም ፣ የተቃዋሚ ድርጅቶች ደጋፊዎች ናችሁ በሚሉ እና በሌሎችም ከስራ ጋር በተያያዘ በሚፈጠሩ ጥፋቶች የተቀጡ ሾፌሮች፣ እስከ 6 ወር ምንም አይነት ስራ እንዳይሰሩ የሚታገዱ” ሲሆን፣ መመሪያው ከወጣ በሁዋላ በርካታ ሾፌሮችና ቤተሰቦቻቸው ለችግር በመዳረጋቸው የስራ ማቆሙ አድማ ተጠርቷል።
አድማውን ተከትሎ የአካባቢው ትራፊክ ፖሊሶች የመኪኖችን ታርጋ እየፈቱ መኪኖችን ያሰሩ ሲሆን፣ ባለሀብቶች በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ መኪኖችን ቅጣት ከፍለው እንዲወስዱ ፣ ካልወሰዱ ግን ንብረታቸው እንደሚወረስ ተነግሯቸዋል። በአድማው የተሳተፉም ሆነ እግድ የተጣለባቸው ሹፌሮች ስራ እንደማይጀመሩ ተነግሮዋቸዋል።
መንግስት ባወጣው መመሪያ አንድ ሹፌር የመንግስትን ትእዛዝ ካላከበረ ወይም ትርፍ ከመጫንና ከተዛማጅ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ከተቀጣ ለ6 ወር ያክል መንጃ ፈቃዱን ይነጠቃል።