ጥር ፲፫(አስራ ሦስት ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ዜጎች የምርጫ ካርድ እንዲያወጡ ጥሪ ያቀረበው የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር፤ <<ምህዳሩ ካልተስተካከለ ምርጫው አንድ ቀን ሲቀረውም ቢሆን ከምርጫ ልንወጣ እንችላለን›› ሲል አስታወቀ።
ትብብሩ ፡<<ነፃነትን የማስመለስ ትግሉን አጠናክረን እንቀጥላለን>> በሚል ርእስ ባወጣው መግለጫ፤ ኢህአዴግና ምርጫ ቦርድ አፈና እና ጫና እያደረጉ ቢሆኑም ነፃነትን ለማስመለስ የያዘውን ግብ ለማሳካት ወደኋላ እንደማይል አረጋግጧል፡፡
‹‹የኢህአዴግ ጨካኝነትና የምርጫ ቦርድ አጋፋሪነት ሊቀጥል ይችላል›› ያሉት የትብብሩ ሊቀመንበር ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት፤ ሆኖም የትግሉ አላማ ኢህአዴግን ማጋለጥ በመሆኑ የሚያስፈልገውን መስዋዕትነት እየከፈሉ ትግሉን እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል፡፡
የትብብሩ ም/ል ሊቀመንበር አቶ ኤርጫፎ ኤርዴሎ በበኩላቸው፦ ‹‹ህዝቡ ካርድ እንዲያወጣ ጥሪ ስናደርግ የፖለቲካ ምህዳሩ ተስተካክሏል እያልን አይደለም፡፡ እኛ አሁንም እያነሳን ያለነው የትግል ጥያቄ ነው፤ የትብብሩ የትግል አላማ ይህን የተዘጋ ምህዳር ማስከፈት ነው፡፡>>ብለዋል።
ትብብሩ በመግለጫው፦‹‹የትግሉ ቀዳሚና ዋነኛ ባለቤት የሆንከው መራጩ ህዝብ፤ ዛሬውኑ በመመዝገብ የሥልጣን ባለቤትነትህን የምታረጋግጥበትንና ይህን አምባገነናዊ ሥርዓት የምትቀጣበትን ‹‹የምርጫ ካርድህ››ን በእጅህ እንድታስገባ›› ሲል፤ ህዝቡ የምርጫ ካርድ እንዲወስድ ጥሪ አቅርቧል።
ይሁንና በአሁኑ ወቅት ትብብሩ እንዲሻሻሉ የሚጠይቃቸው ጥያቄዎች የማይመለሱ ከሆነ እና ምህዳሩ ካልተስተካከለ፤ ምርጫው አንድ ቀን ሲቀረውም ቢሆን ከምርጫው ሂደት ሊወጣ እንደሚችል አስጠንቅቋል፡፡
አቶ ግርማ በቀለ በበኩላቸው እስካሁን ትብብሩ ባደረገው የትግል ሂደት ፤ምርጫ ቦርድ ከኢህአዴግ ጎን እንደቆመ ያረጋገጡበት እንደሆነ ጠቅሰው፤ ሂደቱን ለመወሰን ህዝቡ ምርጫ ካርዱን አውጥቶ መጠባበቅ እንዳለበትና ምርጫ የመግባትና አለመግባት ጉዳይ ለመወሰን ጊዜው ገና መሆኑን ገልጸዋል፡፡