በምርጫ ቦርድና በአንድነት ፓርቲ መካከል የተፈጠረው  ውዝግብ የመጨረሻው ጫፍ ላይ ደርሷል ። ፓርቲው -ጥር 17 ታላቅ የተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ ነው

ጥር ፲፫(አስራ ሦስት ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ምርጫ ቦርድ የውስጥ ጠቅላላ ጉባዔ ጠርታችሁ የውስጥ ችግራችሁን ካልፈታችሁ በመጪው ምርጫ አትሳተፉም የሚል  ውሳኔ በ አንድነትና በመ ኢአድ ፓርቲዎች ላይ ማሳለፉን ተከትሎ አንድነት ፓርቲ  የቦርዱን ውሳኔ ለማሟላት ከሳምንት በፊት  በአስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ  ማካሄዱ ይታወሳል።

 

ይሁንና በወቅቱ ድርጅቱ  በጠራው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ተጋብዞ  ተወካዩን ለመላክ ፈቃደኛ ያልሆነው ምርጫ ቦርድ፤ ፓርቲው በአቋም ተለይተው  ካፈነገጡ ጥቂት የቀድሞ አባላቱ ጋር ተስማምቶ ዳግም የጠቅላላ ጉባዔ እንዲያደርግ  በደብዳቤ ትእዛዝ አስተላልፏል።

ባለፈው ቅዳሜ የተሰበሰበው የአንድነት ብሄራዊ ምክር ቤትም፤ ምርጫ ቦርድ በፃፈው ድብዳቤ ከተወያየ በኋላ ደብዳቤው ህገወጥ ነው ሲል አወግዟል።

ምርጫ ቦርድ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ በተካሄደ ማግስት ሌላ ጠቅላላ ጉባኤ ጥሩ ማለቱንና  ጉባ ዔው ሲጠራ ደግሞ አልታዘብም ማለቱን  ያስታወሱት የጠቅላላ ጉባኤው አባላት፤ አሁን ደግሞ  ለሶስተኛ ጊዜ ሌላ ጠቅላላ ጉባኤ ጥሩ ማለቱ ህገወጥ ተግባር ነው >> በማለት  የቦርዱን አሰራር በ አንድ ድምጽ ኮንነዋል። ተሰብሳቢዎቹ አክለውም፦<< ከእንግዲህ ጠቅላላ ጉባኤ አንጠራም!   ከእንግዲህ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት እና ወደ ህዝቡ ነው የምንወስደው!>> በማለት ወስነዋል።

የአንድነት ፓርቲ  ስራ አስፈፃሚ በምርጫ ቦርድ እና በስርዓቱ የተደቀነበትን የማፍረስ ዘመቻ ለመመከት ግብረ ኃይል ማቋቋሙን የገለጸው ፓርቲው፤ ምርጫ ቦርድና ኢህአዴግ ፓርቲውን ለማስረስ የሚያደርጉትን በመቃወም  ለጥር 17 ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድርግ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ አስታውቋል።

የአንድነት አባለት፣ ደጋፊዎች በጠቅላላ በኢትዮጵያ የስርዓት ለውጥ እንዲመጣ የምንፈልግ ሁሉ በዚህ በአጭር ጊዜ ሰልፎቹ የተሳኩ እንዲሆኑ አስፈላጊውን ርብርብ ያደርጉ ዘንድ ሀገራዊ ጥሪ አቅርቧል።

 

<<በምንም ዓይነት ሁኔታ አንድነት -ለምርጫ ቦርድ ህገወጥ ተግባራት አይምበረከክም>> ያለው ፓርቲው፤  << ፓርቲያችን በምርጫው ይሳተፍም ፤አይሳተፍም፤የምፅዓት ቀን ቀርበዋልና ለንሰሀ ተዘጋጁ እንዲል መፅሐፉ –   ህዝቡን ጫፍ እስከ ጫፍ የማደራጀቱን ስራ ግን ጠንክሮ እንደሚቀጥልበት የማያወላውል ውሳኔ  ማሳለፉን አስታውቀል።

ህዝባዊ ትግሉን ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማሸጋገር ያለውን ታሪካዊ ሃላፊነት ለመወጣት ከመቸውም ጊዜ በላይ ዝግጁ መሆኑን ያሳወቀው አንድነት ፓርቲ፤  አባላቱ፤ ደጋፊዎቹና ህዝቡ አመራሩ ለሚያሳልፈው ውሳኔና እንቅስቃሴ በተጠንቀቅ እንዲጠብቅ ጥሪ አቅርቧል።

ይህ በ እንዲህ እንዳለ ራዲዮ ፋና-ከምርጫ ቦርድ ጋር በመተባበር ዛሬ በሸራተን አዲስ ላሊበላ አዳራሽ ባዘጋጀው ኮንፈረንስ ተጋባዥ ከነበሩት ፓርቲዎች መካከል የአንድነት ፓርቲ ወኪል የነበሩት አቶ አስራትወ ጣሴ መድረኩን ጥለው ወጥተዋል።

ሚኒስትሮችና ከፍተኛ ባለስልጣናት በታደሙበት በዚህ ያዲዮ ፋና መድረክ የውይይት መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት ኢህ አዴግ፣ምርጫ ቦርድ፣ ኢዴፓ እና መድረክ ናቸው።

የአንድነቱ ተወካይ አቶ አስራት መድረኩን ጥለው የወጡት  ጽሁፎቹ ከቀረቡ በሁዋላ ለመናገር ሲዘጋጁ በመድረኩ መሪ በራዲዮ ፋናው ምክትል ስረታ አስኪያጅ በብሩክ ከበደ አማካይነት የተሰጣቸው 3 ደቂቃ ብቻ ነው በመባሉ፣ እንዲሁም ከአንድነት ከተለዩት ጥቂት ሰዎች መካከል አቶ ትእግስቱ የሚባሉት የቀድሞው የፓርቲው አመራር  የ አንድነት ፕሬዚዳንት በሚል ፕሮቶኮል በኮንፈረንሱ እንዲታደሙ በመደረጋቸው ነው።

አንድነት አንድ እንጂ ሁለት ፕሬዚዳንት የለውም ያሉት አቶ አስራት፤ ገዥው ፓርቲ አንድነትን ይበልጥ ውዝግብ ውስጥ ለማስገባትና ለማፍረስ ባሴረበት መድረክ መሳተፍ ፓርቲያቸውን የሚጠቅም ሆኖ እንዳላገኙት ተናግረዋል።  ከአቶ አስራት ጋር ያደረግነውን አጠር ያለ ቃለ ምልልስ በልዩ ፕሮግራም የምናቀርብ መሆኑን እናሳውቃለን