የመኢአድ አባላት በጅምላ እየታፈሱ ነው

ጥር ፲፫(አስራ ሦስት ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በአማራ ክልል  የመላው ኢትዮጰያ አንድነት ድርጅት  አባላት በብዛት እየታሰሩ መሆናቸውን ከስፍራው  አንድ የመኢአድ  አመራር ገለጹ።

የድርጅቱ የ አዲስ አበባ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ አወቀ አባተ  ለኢሳት እንደገለጹት፤በምራብ ጎጃም ዞን  በዳንግላ ወረዳ ጫራ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት የመኢአድ አባላት ወጣት ታጀለ አለኸኝ እና ወጣት የዋንስ ገደቡ፣ እንዲሁም የቡሬ ወረዳ  የ መ ኢአድ ወኪል የሆነው  አቶ አዝመራው ከፋለ  ሰሞኑን  በፖሊሶች ተይዘው ወዳልታወቀ ስፍራ ተወስደዋል።

እንዲሁም በጎንደር ከተማ ቀበሌ 18 ነዋሪ የሆኑት የመኢአድ አባላት ወጣት ተስፋ አስማረና  ወጣት ችሎት ባዜ  በፌደራል ፖሊስ ተይዘው መወሰዳቸውንና  የደረሱበት አለመታወቁን የህዝብ ግንኙነት ሀላሰፊው ተናግረዋል።

በተመሳሳይ  በጃዊ ወረዳ  የመ ኢአድ አባላት የሆኑ በርካታ ወጣቶችም  በፌደራል ፖሊስ  ታፍሰው  የደረሱበት  መጥፋቱን  የገለጹት አቶ አወቀ፤ ስለጉዳዩ የወረዳው የፖሊስ አዛዥ ቢጠየቅም  <<የወሰዳቸው የፌድራል ፖሊስ ነው፤ እኛ የምናውቀው ነገር የለም>>” በማለት ምላሽ መስጠቱን ተናግረዋል።

“መኢአድን በማፈን ትግሉ ማቆም አይቻልም” ያሉት አቶ አወቀ፤  “ትግሉ በ እልህና በቁጭት ይበልጥ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ባለፉት ጥቂት ወራት ብቻ በርካታ የመኢአድ አመራሮች  በማእከላዊ ወንጀል ምርመራ ታስረው እየተሰቃዩ እንደሚገኙ በተደጋጋሚ መዘገቡ ይታወቃል