ታኀሳስ ፳፰(ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ሰሞኑን በጣና ሐይቅና በዙሪባ በሚገኙ የእርሻ መሬቶች ላይ የተከሰተውን አደገኛ አረም ለማየት የተንቀሳቀሰው ቡድን ሃምሳ ሽህ ሄክታር የሚሸፍን የጣና ሐይቅ እና ዙሪያው በእምቦጭ አረም መወረሩን ለመገናኛ ብዙሃን ገልጿል ፡፡ ይህም ለሐይቁ ህልውና አስጊ መሆኑን፤ የተለያዩ ከፍተኛ የገዢው መንግስት አካላትና በዘርፉ ጥናት ያደረጉ ምሁራን ተናግረዋል፡፡
አርሶ አደሮች በበኩላቸው፦” የምናርሰው መሬት ሙሉ በሙሉ በአረሙ በመወረሩ ችግር ላይ ነን ፤ አረሙን ለማጥፋት በተደረገው ዘመቻ መንግስት ድርሻውን አልተወጣም” በማለት አማረዋል፡፡ ጣና ውሃ አዘል በሆኑ መሬቶችና ገባር ወንዞች የተከበበ ከመሆኑ አኳያ- ከእርሻ ቦታዎች የሚወጣው የማዳበሪያ መጠን እጅግ በጣም እየጨመረ መምጣቱ፤ በአንጻራዊነት ጥራት ያለው ውሃ በማግኘት ፋንታ በኬሚካሉ በሚደርስበት ብክለት ለከፍተኛ አደጋ እየተጋለጠ መሆኑን በዘርፉ ጥናት ያካሄዱት ምሁራን እያስጠነቀቁ ነው።
ታይቶ የማይታወቅ አደጋ አንዣቦበታል በተባለው ጣና ሀይቅ ዙሪያ የተሰናዳው ቅንብር በልዩ ፕሮግራም የሚቀርብ መሆኑን እናሳውቃለን።