አንድ የአየር ሃይል አብራሪ ተቃዋሚዎችን  መቀላቀሉ ተሰማ

ታኀሳስ ፳፯(ሃያ ሰባት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ባለፈው ረቡዕ ታህሳስ 15፣ 2007 ዓም ኢሳት 4 የአየር ሃይል አብራሪዎች ወደ ኬንያ ማምራታቸውን በሰበር ዜና ካቀረበ በሁዋላ፣ አንድ ተጨማሪ የአየር ሃይል ባልደረባ ጠፍቶ ተቃዋሚዎችን መቀላለቀሉ ተሰምቷል።

ባለፈው ሮብ የጠፉት የሚግ 23 አብራሪ ሻምበል ገዛሃኝ ደረሰ፣ የኤም አይ 35 ተዋጊ ሄሊኮፕተር አብራሪ ሻምበል ዳንኤል ግርማ፣  የኤም አይ 35 ተዋጊ ሄሊኮፕተር አብራሪ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጠ፣ የኤም አይ 35 ተዋጊ ሄሊኮፕተር ብሩክ አጥናኤ በአጥሩ የደህንነት ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ታውቋል።

ወደ ኬንያ ያመሩት በአሁኑ ጊዜ በጥሩ የደህንነት ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ለኢሳት የደረሰው ዜና ያመለክታል። ባለፉት 3 ቀናት የጠፋው አብራሪ ተቃዋሚዎችን መቀላቀሉ የታወቀ ሲሆን፣ ስሙንና የስራ ድርሻውን በተመለከተ በቅርቡ ይፋ ይሆናል። ባለፈው ሳምንት ግምገማቸውን የጨረሱት የአየር ሃይል አባላት፣ ስለጠፉት አየር ሃይል አባላት መረጃዎችን እንዲየጣወጡ ሲዋከቡ ከቆዩ በሁዋላ፣ ባለስልጣኖቹ ምንም ነገር ለማግኘት ባለመቻላቸው የአየር ሃይል አባላቱን ወደ መለማመጥና መለመን ደረጃ ደርሰዋል።

“ምንድነው የቸገራችሁ? ምን እናሟላላችሁ?” “እስካሁን ላጠፋነውም ይቅርታ አድርጉልን” በማለት  አብራሪዎችን እየተለማመጡ እንደሚገኙ የውስጥ ምንጮች ገልጸዋል። በአየር ሃይል ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የሰራዊቱ ክፍል ውስጥ የሚገኙ ከፍተኛ ማእረግ ያላቸው መኮንኖች ተቃዋሚ ሃይሎችን ለመቀላቀል ጥያቄ እየቀረቡ ቢሆንም፣ ከተቃዋሚዎች በኩል ” ውስጥ ሆናችሁ ታገሉ” የሚል መልስ እየተሰጠ ነው። አንድ ስማቸው እንዳይነገር የፈለጉ የተቃዋሚ አመራር  እንደተናገሩት የሃይል ትግሉን ለመቀላቀል የሚጠይቁ ከፍተኛ መኮንኖች ትግላቸውን በውስጥ ሆነው እንዲያካሂዱ ተነግሯቸዋል።

መንግስት አራት አብራሪዎች አልጠፉም ሲል ማስተባባያ መስጠቱ በድሬዳዋና ሌሎች ምድቦች ያሉ የአየር ሃይል አባላትን በእጅጉ እንዳስገረመ ምንጮች አክለው ገልጸዋል። የአየር ሃይል አባላት  ስርአቱን አናገለግልም በማለት በብዛት መጥፋታቸው የህዝብ ትኩረት ስቦ በሚገኝበት ወቅት፣ መንግስት ትኩረቱን ለማስቀየር በሚመስል መልኩ በግፍ እስር ላይ የሚገኘውን የግንቦት7 ዋና ጻሀፊ አንዳርጋቸው ጽጌን በኢቲቪ አቅርቦ አሳይቷል። ኢቲቪ ያቀረበው ፊልም የተቆራረጠና መልክቱ በግልጽ የማይሰማና አላማው የማይታወቅ መሆኑ፣ በማህበራዊ ድረገጾች ሌላ የመነጋገሪያ አጀንዳ ፈጥሯል።

ባለፉት 6 ወራት ብቻ 15 ልምድ የነበራቸው የአየር ሃይል አባላት ስርአቱን በመተው ተቃዋሚዎችን ተቀላቅለዋል። የአየር ሃይል አዛዦችን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።