መድረክ -ከገዥው ፓርቲ ጋር በአሰቸኳይ መወያዬተ እፈልጋለሁ አለ።

ታኀሳስ ፳፯(ሃያ ሰባት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በመጪው ግንቦት በሚካሄደው ምርጫ ሂደት ላይ ቅሬታዎች አሉኝ ያለው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ፤    ከገዥው ፓርቲ ጋር በአስቸኳይ መወያየት እንደሚፈልግ አስታውቋል፡፡ መድረክ በትናንትናው እለት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ በምርጫ ታዛቢዎችና አስፈፃሚዎች አመራረጥና በምርጫው ለሚሳተፉ ፓርቲዎች ከመንግስት በሚሰጠው የድጐማ ገንዘብ ክፍፍል ላይ ቅሬታ እንዳለው ተናግሯል።

መድረክ አያይዞም፦”ምርጫውን ለማስፈፀምና ለመታዘብ ከፖለቲካ ፓርቲ አባልነት ገለልተኛ የሆኑ ሠዎች መመረጥ ያለባቸው ቢሆንም፤ በቅርቡ የተመረጡት አስፈፃሚዎች አብዛኞቹ የገዥው ፓርቲ አባላት መሆናቸው እየታወቀ “የማንም ፓርቲ አባላት አይደለንም” እያሉ ፈርመው ወደ አስፈፃሚነቱ እንዲቀላቀሉ ተደርጓል” ሲል  ቅሬታውንገልጿል፡፡ መንግስት ለፓርቲዎች የሚሰጠውን ገንዘቡ ለሚመለከታቸው ፓርቲዎች ብቻ በአግባቡ እንዲከፋፈል ያሳሰበው መድረክ፤ “ከመንግሰት ካዝና ወጥቶ ታማኝ ለሚባሉ ፓርቲዎች እየተከፋፈለ ያለው ገንዘብ በአስቸኳይ እንዲቆም እንጠይቃለን” ብሏል፡፡

“ከመንግስት ካዝና የወጣን ገንዘብ ታማኝ ለተባሉ ፓርቲዎች ብቻ ማከፋፈል- ከፖለቲካ ሙስና ተለይቶ አይታይም” ሲልም ድርጊቱን ኮንኗል። የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ፤የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል አይደለም። ምርጫ ቦርድ፤ ፓርቲዎች በፓርላማና በክልል ምክር ቤት ባላቸው መቀመጫ እንዲሁም በሚያቀርቧቸው እጩዎች ብዛትና የሴቶች ተሳሣትፎን መሠረት አድርጐ ገንዘቡን ለማከፋፈል መወሰኑን የተቃወመው ፓርቲው፤ በተለይ የምክር ቤት መቀመጫ የሚለው መስፈርት ኢህአዴግን ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመ ነው ብሏል፡፡

“በምክር ቤት መቀመጫ በሚለው የቦርዱ ቀመር መሰረት ኢህአዴግ ለብቻው 55 በመቶውን ድርሻ ሲያገኝ፤ ቀሪው 45 በመቶ 59 ፓርቲዎች የሚከፋፈሉት ይሆናል”