ታኀሳስ ፲፭(አስራ አምስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በዘላለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ በሽብርተኝነት ወንጀል የተከሰሱት የሰማያዊ፣ የአንድነትና አረና አመራሮች ከሌሎች 6 ተከሳሽ ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን ልደታ በሚገኘው 19ኛው ወንጀል ችሎት ቀርበው በእስር ቤት ውስጥ ስለሚደርስባቸው እንግልትና የደህንነት ስጋት ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ አሰምተዋል።
የተከሳሾች ቤተሰቦች እስረኞችን ለመጠየቅ በሚሄዱበት ጊዜ በተለየ መዝገብ መመዝገባቸውን በመቃወም ለፍርድ ቤት ባሰሙት አቤቱታ መሰረት ፣ ማረሚያ ቤቱ ” እስረኞች እንደማንኛውም እስረኛ መያዛቸውንና የተለየ ችግር እንዳልገጠማቸው” በጽሁፍ መልስ መስጠቱን ፍርድ ቤቱ ጠቅሶ፣ የማረሚያ ቤቱን መልስ እንደሚቀበለው ለእሰረኞችና ለጠበቆች ገልጿል።
የእስረኞቹ ጠበቃ ተማም አባ ቡልጉ ደንበኞቻቸው በእስር ቤት ውስጥ ተገቢ ያልሆነ ማንገላታት እየደረሰባቸው መሆኑን ለዚህም ማሳያ ታህሳስ 12 እና 13 ከሌሊቱ 8 ሰአት ጀምሮ በክፍላቸው ወስጥ ድንገተኛ ፍተሻ መደረጉን ፣ ይህንንም ተከትሎ የግል ማስታወሻዎቻቸው፣እንዲሁም በማዘጋጀት ላይ ያሉት የክስ መቃወሚያ እና ገንዘብ እንደተወሰደባቸው ገልጸዋል። በደንበኞቻቸው ላይ እየተፈጸመ ያለው ህገወጥ ድርጊት ለህይወታቸው አስጊ መሆኑን የገለጹት ጠበቃ ተማም፣ ፈታሾቹም የማረሚያ ፖሊሶች ሳይሆኑ የደህንነት አባላትና ፌደራል ፖሊሶች ናቸው ብለዋል።
አቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ-በአቶ ተማም ለቀረበው አቤቱታ᎒ ማረሚያ ቤቱ ዜጎች ታንጸውና ታርመው እንዲወጡ የሚያደርግ የራሱ ሆነ አሰራር አለው በማለት የተቃውሞ መልስ ሰጥተዋል። አቶ ተማም በበኩላቸው ፍተሻው በሌሊት መካሄዱን ፣ ፍተሻው የተካሄደውም በማረሚያ ቤት ፖሊሶች ሳይሆን በፌደራል ፖሊስና በደህንነቶች መሆኑን በማስረዳት የአቃቢ ህግን መቃወሚያ ውድቅ አድርገዋል። ጠበቃው አክለውም የተወሰዱ እቃዎች እንዲመለሱላቸው ጠይቀዋል።
ዳኞች “አቶ ተማም የሰጡት አስተያየት ተገቢ አይደለም፣ ማረሚያ ቤቱ በእስረኞች ላይ የበቀል እርምጃ እንዲወስድ የሚያበረታታው ነው” በማለት ሲናገሩ፣ በዳኞች ንግግር የተበሳጨው የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ሀብታሙ አያሌው ዳኛውን<< የተናገሩት ትክክል አይደለም፣ በህይወቴ ላይ አደጋ አንዣቦብኛል፣ እርስዎ ደግሞ የበቀል እርምጃ እንዲወሰድብን እያሳሰቡ ነው ፣ ይህ ትክክል አይደለም፣ ከዚህ ስንመለስ ምን እርምጃ እንደሚወሰድብንም እርግጠኞች አይደለንም። ፍርድ ቤቱ ከእስር ቤቱ ጋር ሆኖ የእኛን አቤቱታ ውድቅ በማድረጉ አቤት የምንልበት ሌላ አማራጭ አጥተናል” ብሎአል።
ዳኞችም በሃብታሙ ለቀረበው አቤቱታ ህጉን ተንተርሰን ነው የምንናገር በማለት ፣ለታህሳስ 24 ተለዋጭ ቀጠሮ በመስጠት የእለቱን ችሎቱን አጠናቀዋል።