ኀዳር ፲፩(አስራ አንድ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ቢቢሲ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽንን ጠቅሶ እንደዘገበው ባለፉት 37 ቀናት ከ6 ሺ ያላነሱ ኤርትራውያን ብሄራዊ ውትድርናን በመሸሽ ተሰደዋል። ኮሚሽኑ እንደሚለው የስደተኞች ቁጥር ካለፈው ወር ጋር ሲነጸጻር በእጥፍ ጨምሯል።
የኤርትራ መንግስት በበኩሉ ብሄራዊ ወትድርና ዘመቻ ያስፈለገው በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ድንበር አካባቢ ያለው ውጥረት እየጨመረ በመምጣቱ እንደሆነ ገልጿል። ሁለቱ አገሮች ከ14 አመታት በፊት ባደረጉት ጦርነት ከ100 ሺ ያላነሰ ህዝብ አልቋል።
የኢህአዴግ መንግስት ከኤርትራ ጋር ለመታረቅ ተደጋጋሚ ጥያቄ ሲያቅርብ መቆየቱን አቶ መለስና አቶ ሃይለማርያም መናገራቸው ይታወቃል። ይሁን እንጅ ኤርትራ የኢትዮጵያ መንግስት በአለማቀፍ ፍርድ ቤት በተወሰነው መሰረት ባድሜን ለቆ ካልወጣ፣ እርቅ የሚባል ነገር አይኖርም በማለት በአቋሟ እንደጸናች ነው።