በአፋር በጎርፍ የተፈናቀሉት ድጋፍ አልተደረገልንም አሉ

ኀዳር ፲፩(አስራ አንድ) ቀን ፳፻፯ / ኢሳት ዜና :-በላይኛው አዋሽ ተፋሰስ ከመስከረም 28 ቀን 2007 ጀምሮ በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት የተፈናቀሉ በሺ የሚቆጠሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ከእለት ዕርዳታ ባለፈ ድጋፍ እየተደረገላቸው አለመሆኑን ገለጸዋል፡፡

የአካባቢው ተወካይ እንደገለጹት መንግስት በአካባቢው የገነባው የዝናብ መከላከያ ደረጃውን የጠበቀ ባለመሆኑ ምክንያት በጎርፍ በቀላሉ መሰበሩን ጠቅሰው በዚህ ምክንያት ማሳ ላይ የነበረ ምርታቸውን ጨምሮ መኖሪያ ቤቶቻቸው በጎርፍ መወሰዱን ጠቅሰዋል፡፡

አደጋው ከተከሰተ በሃላ ወደእለት  ጉርስ ተረጂነት መሸጋገራቸውን የጠቀሱት የነዋሪዎቹ ተወካይ  ይሁንና እስካሁን  በዘላቂነት ለማቋቋም የታሰበ ነገር ስለመኖሩ እንዳልተነገራቸው ገልጸዋል፡፡

ከአዋሽ ተፋሰስ ባለስልጣን የተገኘው መረጃ  በአዋሽ ወንዝ ሙላት የተከተለው የጎርፍ እደጋ ከ1991 ወዲህ የተከሰተ ከባድ አደጋ እንደሆነና የጎርፍ መከላከያውን ሰብሮ ማለፍ በመቻሉ ምክንያት በንብረት ላይ የከፋ ጉዳት መድረሱን ያመለክታል፡፡