ኀዳር ፩(አንድ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከሰሜኑ የአገሪቱ ክፍሎች የታፈኑ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ወደ ማዕከላዊ መዛወራቸውን ነገረ ኢትዮጵያ ዘግቧል፡፡ በሰሜን ጎንደር ዞን የሰማያዊ ፓርቲ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ አግባው ሰጠኝ ፣ የምእራብ አርማጭሆ የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ሰብሳቢ
አቶ አንጋው ተገኝ ትናንት ወደ ማዕከላዊ መወሰዳቸውን ጋዜጣው ዘግቧል። ሌሎች የተቃዋሚ አመራሮች ወደ ማእከላዊ ይወሰዱ አይወሰዱ ጋዜጣው አላብራራም።
ባለፈው ሳምንት በትግራይ ክልል በምዕራባዊያን ዞን ቃፍታ ሁመራ ወረዳ ዳንሻ ከተማ የአረና ፓርቲ የማእከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ዘነበ ሲሳይ ፣ በሁመራ የአረና የቁጥጥር ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ አማረ ተወልደ ፣ በአማራ ክልል ምዕ/ጎጃም ዞን ደጋ ዳሞት ወረዳ የአንድነት ፓርቲ ሰብሳቢ አቶ ጥላሁን አበበ እና ሶስት
የድርጅቱ አባላት፣ በምእራብ ጎጃም በፍኖተሰላም ከተማ የመኢአድ ሰብሳቢ አቶ ዘሪሁን ብሬ ፣ የምኣረብ አርማጭሆ የአንድነት ጸሃፊ አቶ አባይ ዘውዱ፣ እንግዳው ዋኘው፣ የመተማ ሰብሳቢ አቶ በላይነህ ሲሳይ ተይዘው ታስረዋል። የድርጅት አመራሮቹ በተያዙበት ወቅት ከፍተኛ ድብደባ ተፈጽሞባቸዋል።