በዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ የሟች ኢትዮጵያዊት ቤተሰብ ገንዘብ  ተቀብለው ገዳዮች ከእስር እንዲወጡ ማድረጋቸው ተዘገበ

ኀዳር (አንድ) ቀን ፳፻፯ / ኢሳት ዜና :- ገልፍ ኒውስ ባወጣው ዘገባ 4 ወንዶች አንዲት ኢትዮጵያዊትን አአስገድደው መኪና ላይ ከጫኑዋት በሁዋላ በየተራ ደጋግመው በመድፈርና በመኪናቸው ገጭተው በመግደል በላዩ ላይ ድንጋይ በማስቀመጥ ለማምለጥ ሞክረዋል።

ግለሰቦቹ ተይዘው ፍርድ ቤት ከቀረቡ በሁዋላ የጄራጂ ፍርድ ቤት በግለሰቦቹ ላይ የሞት ፍርድ ለማስተላለፍ በሂደት ላይ ነበር። ይሁን እንጅ ዳኛ አብዱላህ የሱፍ አል ሻሚሲ ፣ ላለፉት 5 አመታት በእስር ላይ የቆዩት ገዳዮች በዋስ እንዲፈቱ ፈቅደዋል።

የገዳዮቹ ጠበቃ እንደተናገሩት ገዳዮቹ ለሟች ቤተሰብ 100 ሺ  ዲሪያ ወይም 27 ሺ ዶላር የደም ካሳ ክፍያ ከከፈሉ በሁዋላ በዋስ እንዲወጡ ተደርጓል።

ጠበቃው አክለውም፣ የሟች ቤተሰብ የሞት ፍርድ እንደፈረድ ሲጠይቁ የነበረውን መተዋቸውንና የደም ካሳውንም እንደተቀበሉ ዱባይ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ተገልጾልናል ብለዋል። የሟች ቤተሰቦች ከዚህ ቀደም ይዘውት የነበረውን አቋም መለወጣቸው አስገራሚ መሆኑን ጋዜጣው ዘግቧል።

ከ4 አመታት በፊት የአገሪቱ  አንደኛ ደረጃ ፍርድ ቤት በወንጀለኞች ላይ የሞት ፍርድ ፈርዶ ነበር።

የኢትዮጵያ ኢምባሲ ገንዘቡን ለበተሰቡ መስጠት አለመስጠቱን ለማረጋገጥ አልተቻለም። የሟች ቤተሰብ አባላትም ገንዘብ ስለመቀበልና አለመቀበላቸው የገለጹት ነገር የለም። ዘገባው በልጅቱ ወላጆች በኩል የተሰጠውን አስተያየት አላከተተም።