ሰኔ ፱(ዘጠኝ)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር በተያያዘ በኦሮምያ ተነስቶ የነበረውን ተቃውሞ ተንተርሶ ከተያዙት በሺ ከሚቆጠሩ ወጣቶች መካከል የተወሰኑት ከእስር ሲለቀቁ፣ አብዛኞቹ አሁንም በእስር ላይ ይገኛሉ።
የክልሉ ወኪላችን እንደሚለው በወለጋ፣ በአንቦና አጎራባች ወረዳዎች የታሰሩ በርካታ ወጣቶች አሁንም ፍትህ አጥተው በእስር ላይ ሲሆኑ በቡራዩ ታስረው ከነበሩት መካከል 3ቱ ዛሬ በዋስ ተለቀዋል። ጋዲሳ ጉደታ፣ ቱፋ በክሩ እና ጉዲሳ ድሪባ የተባሉት ተከሳሾች ዛሬ ከእስር ሲለቀቁ፣ ዳውድ ሃሰን የተባለው ደግሞ ከሳሽ አጥቶ ወደ እስር ቤት እንደሚለስ ተደርጓል። የዞኑ ፍርድ ቤት የዳውድ ክስ አይመለከተኝም ያለ ሲሆን፣ የወረዳው ፍርድ ቤትም ክስ እንደማይመሰርትበት አስታውቋል። ዳውድ ፍትህ አጥቶ በእስር ቤት እንዲቆይ በመደረጉ በከፍተኛ ሁኔታ የስሜት መረበሽ አጋጥሞት እንደነበር ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ሰዎች ለወኪላችን ገልጸውለታል።
በደዴሳና በአምቦ እስር ቤቶች የታሰሩ ወጣቶች አሁንም በፍትህ እጦት እየተሰቃዩ መሆኑን ወኪላችን አክሎ ገልጿል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአዲስ አበባ መስተዳድር በከተማዋ አዲስ ማስተር ፕላን ዙሪያ ውሳኔ ሰጥቶ ወደ ተግባር ለመንቀሳቀስ አለመቻሉን የውስጥ ምንጮች ገልጸዋል።
እንደምንጮች ገለጻ ከፍተኛ ተቃውሞ ያስነሳውን የከተማዋን ካርታ ከመጪው ምርጫ በፊት ተግባራዊ ማድረግ የአካባቢውን ህዝብ ቁጣ የሚቀሰቅስ በመሆኑ እስከ ምርጫ 2007 ጉዳዩን ላለማንሳት ሊወስን ይችላል።