ግንቦት ፭ (አምስት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር በተያያዘ የህወሃት አጀንዳ ነው በማለት ተቃውሞ ሲያሰሙ የነበሩትን የኦህዴድ አባላት ለማሰር እንቅስቃሴ መጀመሩን ከኦህዴድ ምንጮች የደረሱን ዜና አመለከተ።
ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይገለጥ የፈለጉት እነዚህ አባላት እንደተናገሩት፣ ድርጅቱ አዲሱን የአዲስ አበባ ፕላን በተመለከተ አባላቱ እንዲወያዩበት ቢያስደርግም፣ በውይይቱ ወቅት የተቃውሞ ሃሳባቸውን ሲያሰሙ የነበሩትን ሰዎች ማሰር ተጀምሯል። በርኴታ የድርጅቱአባሎች ደግሞ ከእስራት ለመሸሽ መደበቃቸው ታውቋል።
ኦህዴድ የህወሃት ደጋፊና የህወሃት ተቃዋሚ በሚል ከሁለት መከፈሉን ተከትሎ የህወሃት ደጋፊው ወገን ደጋፊ ያልሆነውን ወገን እያሳደደው መሆኑን ምንጮች አክለው ገልጸዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በተለያዩ የኦሮምያ አካባቢዎች ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት የሚደረገው ጥረት ፣ የህወሃት ደጋፊ በሆኑ የኦህዴድ አባላት ተጠናክሮ ቀጥሎአል።
ኢህአዴግ ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር በተያያዘ የተነሳበትን ተቃውሞ የትኩረት አቅጣጫ ለማስቀየር ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት የሌለውን የብሄር አጀንዳ በማንሳት ብሄሮች እርስ በርስ እንዲጣሉ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑን አባሎቹ ተናግረዋል።
በዩኒቨርስቲዎች ሆን ተብሎ አሉባልታ የሚነዙ ካድሬዎች መሰማራታቸውን እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎች በቡድን የተደራጁ ስራ አጥ ወጣቶችንበሌሊት ወደ ሌሎች ብሄር ተወላጆች ቤት በመላክ ግጭት እንዲያነሱ በኳድሬዉች ግፊት እየተደረገመሆኑን እነዚህ ወገኖች አክለው ገልጸዋል።
በምስራቅ እና በምእራብ ወለጋ ኦህዴድ ያደራጃቸው ወጣቶች የሰዎችን ቤቶች እየመረጡ በሌሊት ከመደብደብ ጀምሮ እስከ ማቃጠል መድረሳቸውን እንዲሁም ንብረቶችን እየዘረፉ እንደሚገኙ የሚናገሩት አባሎቹ፣ ህዝቡ በትእግስትና በተለመደው የመከባበር ባህሉ ይህን ችግር እንዲያልፈው አሳስበዋል።
በሌላ ዜና ደግሞ በድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩ ከመቶ በላይ ተማሪዎች ሲለቀቁ፣ 40 ተማሪዎች ግን አመጹን ከቅስቅሳችሁዋል በሚል በእስር ላይ እንዲቆዩና ምርምራ እንዲደረግባቸው ፖሊስ መወሰኑ ታውቋል።
በተመሳሳይ ዜና ከሃሮማያ ዩኒቨርስቲ የወጡትን ተማሪዎች አስጠግተው የነበሩ ቤተክርስቲያኖች፣ ተማሪዎቹን እንዲያስወጡ _ክልሉን በሚመራው የምስራቅ እዝ ወታደራዊ አዛዦች ትእዛዝ ተሰጥቷቸው እንደነበር የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
ማንነታቸውን ያልገለጹ የምስራቅ እዝ ባለስልጣናት ቤተከርስቲያኑዋ በአስቸኳይ ተማሪዎችን እንድታስወጣ ትእዛዝ ከሰጡ በሁዋላ ተማሪዎቹንሸራ በለበሱ መኪኖች ተጭነው መውሰዳቸውን ጉዳዩን በቅርበት ከሚከታተሉ ወገኖች የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
በሃሮማያ ዩኒቨርስቲ ሰኞ እለት ትምህርት ቢጀመርም በግቢው የሚገኙ ተማሪዎች ቁጥር አሁንም እጅግ አነስተኛ ነው።
በኦሮምያ ክልል ያለውን የጸጥታ ችግር በተመለከተ የክልሉን ፖሊስ ለማነጋገር ተደጋጋሚ ሙከራ ብናደርግም አልተሳካልንም።