አምነስቲ በኦሮምያ ግድያ የፈጸሙት ለፍርድ እንዲቀርቡ ጠየቀ

ግንቦት ፭ (አምስት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-አለምአቀፉየሰብአዊ መብቶች ተከራካሪ ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባወጣው መግለጫ ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር በተያያዘ የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ በርካታ ሰዎች መገደላቸውን ገልጿል። በመዳ ወላቡ ዩኒቨርስቲ 3፣ በጉደርና በአምቦ ከ15 በላይ ሰዎች መገደላቸውን አውስቷል::አብዛኞቹ ሟቾች ተማሪዎች እና መምህራን መሆናቸውን የተለያዩ የአይን እማኞችን በማነጔገር  በሪፓርቱ ያሰፈረውአምነስቲየሟቾች ቁጥር በገለልተኛ ወገኖች ቢጣራ ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችልም ገልጿል።

ከሟቾች መካከል የ11 አመት ህጻናት እንደሚገኙበት የገለጸው አምነስቲ፣ መንግስት ከሚገባው በላይ ሃይል መጠቀሙንም ጠቁሟል።

በተለያዩ የኦሮምያ አካባቢዎች የታሰሩት ሰዎች ቁጥር በሺዎች እንደሚቆጠር የኦሮሞ ፌደራሊስት ንቅናቄን በዋቢነት ይፋ አድርጓል።

የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት በተለያዩ አካባቢዎችና በዩኒቨርስቲዎች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የጸጥታ ሃይሎችን ማሰማራታቸውን አምነስቲ አክሎ ገልጿል።

የኢትዮጵያ መንግስት_የጸጥታ ሃይሎች የወሰዱት ከልክ ያለፈ የሃይል እርምጃ በገለልተኛ ወገኖች እንዲጣራ እንዲያደርግ አንዲሁምአጥፊዎቹ ለፍርድ እንዲቀርቡና የታሰሩት  እንዲፈቱ  ድርጅቱ ጠይቋል።