መንግስት 22 ነጋዴዎችን በሽብረተኝነት ወንጀል ከሰሰ

ግንቦት ፭ (አምስት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከወራት በፊት በሃረር የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ፣ የንግድ ድርጅታቸው የተቃጠለባቸው 22 ነጋዴዎች ሁከት በማስነሳት የተከፈተባቸው ክስ ወደ ወደ ሽብርተኝነት በመለወጡ፣ ዋስትና ተከልክለው በሃረሪ እስር ቤት እንዲቆዩ መደረጉን የኢሳት ዘጋቢ ገልጿል።

የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ነጋዴዎች በዋስ እንዲለቀቁ ውሳኔ  አሳልፎ የነበረ ቢሆንም፣ ፖሊስና አቃቢ ህግ ክሱን ወደ አሸባሪነት በመለወጣቸው  ነጋዴዎቹ ከእስር ቤት እንዳይወጡ ተደርጓል። ከእስረኞቹ መካከል 2ቱ ሴቶች ሲሆኑ አንደኛዋ በድበደባ ወቅት ማህጸኗ አካባቢ በመረገጡዋ በከፍተኛ ህመም እየተሰቃየች መሆኑን ዘጋቢያችን ገልጿል።

ዘጋቢያችን እንደገለጸው በእስር ላይ የሚገኙት ነጋዴዎች ድርጅታቸው ተቃጥሎባቸው ለኪሰራ መዳረጋቸው ሳያንስ አሁን ደግሞ በሽብረተኝነት ተከሰው የወስትና መብት መከልከላቸው በክልሉ ውስጥ የተንሰራፋውን ስርአት አልበኝነት ያሳያል በማለት አስተያየት ሰጪዎች ጠቅሶ ዘግቧል።

“ሀረር ከተማ ተረስታለች” የሚሉት አስተያየት ሰጪዎች፣ አስተዳዳሪዎቹ በነዋሪዎች መካከል ግልጽ የሆነ አድልዎ የሚያደርጉ በመሆኑ የከተማዋ ችግር እየተባባሰ መምጣቱ” ገልጸዋል።