የደቡብ ሱዳን መሪ በሚቀጥለው አመት ምርጫ እንደማይደረግ አስታወቁ

ግንቦት ፭ (አምስት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ሳልቫ ኪር ይህን የተናገሩት አዲስ አበባውን የሰላም ስምምነት ፈርመው ከተመለሱ በሁዋላ ነው።

ፕሬዚዳንቱ በሚቀጥለው አመት ሊካሄድ የታሰበው ምርጫ ለሁለት አመታት የተራዘመው ለሰላም ስምምነቱ እድል ለመስጠት ነው ብለዋል።

የሰላም ስምምነቱን የፈረምኩት ተገድጄ ነው ያሉት ኪር፣ ተገደው የፈረሙትን የሰላም ስምምነት ለማክበር ቃል ገብተዋል።

አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ “ይህን ስምምነት የማትፈርሙ ከሆነ አስራችሁዋለሁ እንዳሏቸው” የገለጹት ሳልቫ ኪር፣ ሙሉውን ሰነድ እንዳላነበቡት ገልጸዋል።

በሰላም ስምምነቱ  ሁለቱን መሪዎች ፊት ለፊት ለማገናኘት እቅድ እንደነበረ ቢገልጹም፣ ይህ እንዳልተሳካ ሳልቫኪር ተናግረዋል።

ሳልቫኪር በኢትዮጵያ ላይ ያሰሙት ክስ  በኢትዮጵያ እና በደቡብ ሱዳን መካከል ያለውን ግንኙነት እንዳያሻክረውና የኢትዮጵያን የአደራዳሪነት ሚና ጥያቄ ውስጥ እንዳይጥለው ተሰግቷል።