ግንቦት ፩ (አንድ)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የአፋር ሰብአዊ መብት ድርጅት ከኢትዮጵያ ታስክ ፎርስ ጋር በመተባበር ባዘጋጀው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ የተገኙ ኢትዮጵያውያን ሰሞኑን በኦሮሞ፣ በአፋር፣ በጎንደር እና በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የተፈጸሙት ግድያዎች በጽኑ አውግዘዋል።
ከአስተባባሪዎች አንዱ ሆኑት ዶ/ር ኮንቴ የኢትዮጵያውያኑን ጥያቄ ለአውሮፓ ህብረት ባለስልጣናት ማቅረባቸውንና በሚቀጥለው ሳምንትም ከህብረቱ የውጭ ግንኙነት ሃላፊ ካተሪና አሽተን ጋር ለመገናኘት ቀጠሮ መያዙን ገልጸዋል።
የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ የታሰሩትን ጋዜጠኞችና ጸሃፊዎች አስመልክቶ መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል።
በኖርዌይ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም እንዲሁ የተቃውሞ ሰልፍ ማድረጋቸውን ዘጋቢያችን ገልጿል።
በዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት በኖርዌይ አስተባባሪነት የተጠራው የሰላማዊ ሰልፍ በኦሮሚያ ክልል በከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና በነዋሪዎች ላይ የተፈጸመውን ግድያ አውግዟል።
ሰልፈኞቹ የተለያዮ ወቅታዊ መፈክሮችን በማሰማት ወደ ኖርዌጅያን ፓርላማ ያመሩ ሲሆን ኖርዌይ ከ መንግስትጋር ያላትን ግንኙነት እንድትመረምርና የታክስ ከፋዩ ኖርዌጅያን እንዲሁም የኖርዌይ ነዋሪ ኢትዮጵያውያን ለኖርዌይ መንግስት የሚከፍሉት ታክስ ለንጹሃን ዜጎች ህይወት ማጥፍያ መዋሉን ተቃውመዋል።
በሰላማዊ ሰልፉ ላይ የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ የድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ ፣ የጋራ መድረክ ፣ የኢትዮጵያ ስደተኞች ማህበር በኖርዌይ ፣የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ እና የኢትዮጵያ ማህበር በኖርዌይ ተወካዮች ንግግሮችን አድርገዋል።
የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ የድጋፍ ድርጅት በኖርዌይ ሊቀ መንበር አቶ ዮሐንስ አለሙ የታሰሩ ወጣት ፣ የኦሮሞ ተማሪዎች በአስቸኳይ እንዲፈቱ የእነዚህ የወጣት ተማሪዎችና ሕዝብ ደም በከንቱ መቅረትእንደማይገባው ተናግረዋል። ድርጊቱን የፈጸሙት አንባገነኖች በአስቸኳይ ለፍርድእንዲቀርቡ በመጠየቅ ስርአቱን ለማስወገድ በጽናት ከሚታገሉ ድርጅቶች ጎን ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንዲቆም አሳስበዋል።
የስርአቱ አገልጋዮች የሆኑ የመከላከያ እንዲሁም የፖሊስ አባላት እየተገደሉ ያሉት ንፁሃን ወንድሞቻቸው እና እህቶቻቸው መሆናቸውን ተገንዝበው ከአድር ባይነት ወተው ከብዙሃን ወገኖቻቸው ጋር እንዲቆሙ በማሳሰብ የድርጅቱን የአቋም መልክት ለኖሮዊጅያን ምክር ቤት ተወካይ አስረክበዋል።
የምክር ቤቱም ተወካይ በኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያለውን ውጥረት በቅርበት እየተከታተሉት መሆኑን እና መልዕክታቸውንም በምክር ቤት ውስጥ ለሚመለከታቸው ሁሉ አስተላልፈው እንደሚወያዩበት መግለጻቸውን አበበ ደመቀ ከኖርዌይ ዘግቧል።