ሚያዚያ ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በካተሪና አሽተን የሚመራው የአውሮፓ ህብረት የውጭ ግንኙነት ክፍል በጋዜጠኞች ፣ ጸሃፊዎችና ፖለቲከኞች ላይ እየተካሄደ ያለው እስር እንዳሳሰበው ገልጿል።
የአውሮፓ ህብረት ሁሉንም ወገኖች ያቀፈ ውይይት እንዲደረግ እና የተለያዩ ድምጾች የሚሰሙበት መድረክ እንዲፈጠር ጠይቋል።
ህብረቱ የጋዜጠኞችና ጸሃፊዎች መታሰር እንዳሳሰበው ከመግለጽ በተጨማሪ ጉዳያቸው በነጻ ፍርድ ቤት እንዲታይ፣ ተጠርጣሪዎቹ ከቤተሰቦቻቸው ጋር የሚገናኙበት መንገድ እንዲመቻችላቸው ጠይቋል። ተጠርጣሪዎቹ በማእከላዊ እስር ቤት ከሰው እንዳይገናኙ ተደርጎ መታሰራቸውን የገለጸው ህብረቱ ፣ እስረኞቹ ስላሉበት ሁኔታ ማብራሪያ እንዲሰጠውም ጠይቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በጄኔቫ ስዊዘርላንድ በመካሄድ ላይ ባለው የሰብአዊ መብት አያያዝ ጉዳይ ላይ በርካታ አገሮች የኢትዮጵያ መንግስት የሰብአዊ መብት አያያዙን እንዲያሻሽል የሚጠይቁ አስተያየቶችን አቅርበዋል።
የመከላከያ ሃይሎች በኦሮሞ ተማሪዎች ላይ የወሰዱት እርምጃ እንዲጣራ ኮስታሪካ፣ ፊንላንድ እና ሞንቴኔግሮ ሲጠይቁ፣ አውስትራሊያ፣ ቤልጂየም፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ ሜክሲኮ፣ ናይጀሪያ፣ ስዊድን፣ ዩናይትድ ኪንግደምና ዩናይትድ ስቴትስ ኢትዮጵያ በህገመንግስቱ ያሰፈረችውን ሃሳብን በነጻነት መግለጽ፣ የመደራጀትና የመሰብሰብ መብቶችን እንድታከብር ጠይቀዋል።
አውስትራሊያ፣ ኦስትሪያ፣ ቤልጂየም፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ ፈረንሳይ፣ ሜክሲኮ ኔዘርላንድስ፣ ኖርዌይ፣ ስሎቫክ፣ ስሎቫኒያ፣ ስዊድን እና ስዊዘርላንድ ሽብረትኝነትን እንደገና እንደሚለከተው፣ የጋዜጠኝነት ስራ ከሽብረተኝነት ጋር እንዳያይዝ፣ ሲጠይቁ፣ አሜሪካ በበኩለዋ የሽብረተኝነት ህጉ ለፖለቲካ ፍጆታ እየዋለ መሆኑን ተቃውማለች። የጄክ ሪፐብሊክ ኢትዮጵያ ያሰረቻቸውን ጋዜጠኞች በሙሉ በአስቸኳይ እንድትፈታ ጠይቋል። ኢስቶኒያ ፣ አየር ላንድና ደቡብ ኮሪያ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በኢንተርኔት ላይ የምታደርገውን ስለላ እንድታቆም ጠይቀዋል።
ኦስትሪያ፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ ዴንማርክና ፈረንሳይ ኢትዮጵያ የፕሬስ ህጓን እንድታሻሽልና አለማቀፍ መስፈርት ያሟላ እንዲሆን ጠይቀዋል።
አፍሪካዊቷ አገር ቦትሰዋና በበኩሉዋ በኢትዮጵያ ዳኞች ላይ የሚደርሰው ማስፈራራት፣ ወከባና ከስራ ማባረር እንዳሳሰባት ተናግራለች። ስዊዘርላንድም የፍትህ ስርአቱ እንዲስተካከል ጥያቄ አቅርባለች። አርጀንቲና፣ ፈረንሳይ፣ ፓራጉዋይና ቱኒዚያ ኢትዮጵያ ስለሚታፈኑ ሰዎች የሚደነግገውን ህግ እንድትፈርም መክረዋል።
በርካታ አገሮች በኢትዮጵያ ያለው የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዳሳሰባቸው የገለጹ ሲሆን፣ የቼክ ሩፐብሊክ አቋም ያልተጠበቀ መሆን ጉዳዩን አስገራሚ አድርጎታል።
በሌላ ዜና ደግሞ ስቱዲዮ ከመግባታችን ጥቂት ቀደም ብሎ ዞን ዘጠኝ እየተባለ በሚጠራው የፌስ ቡክ ስም የሚጽፉ ወጣቶች ከታሰሩ ከ10 ቀናት በሁዋላ ፍርድ ቤት ቀርበው ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆባቸዋል።
ፍርድ ቤት የቀረቡት 3 ጋዜጠኞችና 3 ጸሃፊዎች መሆናቸውን ለማወቅ ተችሎአል።