የመንግስት ካድሬዎች በኦሮምያ የተነሳውን ግጭት የብሄር ግጭት ለማስመሰል ዘመቻ መጀመራቸው ታወቀ።

ሚያዚያ ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ኢሳት ከኦህዴድ ምንጮች ባገኘው መረጃ ተንተርሶ የገዢው ፓርቲ ካድሬዎች በአማራና በኦሮሞ ህዝብ መካከል ልዩነትን በመዝራት  ሁለቱን ታላላቅ ብሄሮች ለማጋጨት ያቀዱትን ሴራ ይፋ ካደረገ በሁዋላ፣ በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች የተሰማሩ የገዢው ፓርቲ ካድሬዎች የአማራና ኦሮሞ ወጣቶች እንዲጋጩ ከፍተኛ ቅስቀሳ በማድረግ ላይ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሎአል።

በሃሮማያ እና በድሬዳዋ ዩኒቨርስቲዎች አንዱን ብሄር የሚያጥላሉ ንግግሮች ሆን ተብሎ ተልእኮ በተሰጣቸው ካድሬዎች እየተነገሩ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲም ተመሳሳይ ልዩነት ለመፍጠር እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል።

ካድሬዎቹ በቅርቡ በባህርዳር ከተማ በተካሄደው የስፖርት ቬስቲቫል ላይ አማራ ኦሮሞዎችን ተሳድቧል የሚል ወሬ በመንዛት የኦሮሞዎችን ስሜት ለመቀስቀስ እየሞከሩ መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል። ህወሃት ሆን ብሎ ያሰማራቸው ጥቂት ካድሬዎች በባህርዳር ያሰሙትን ዘለፋ ሆን ብሎ የመላው አማራ ህዝብ አቋም አድርጎ በማድረግ ግጭት ለመፍጠር የሚንቀሳቀሰው ህወሃት ፣ የአብዛኛውን ህዝብ ትኩረት ባያገኝም በወጥመዱ ውስጥ የገቡ ጥቂት ተማሪዎች፣ የህወሃትን አጀንዳ እያራገቡ መሆኑን ምንጫችን ገልጿል።

በአገራችን እየታየው ያለው ሁኔታ አስፈሪ መሆኑን እና ህዝቡ ለዘመናት ተቻችሎና ተከባብሮ እንደኖረው ሁሉ አሁንም በካድሬዎች ቅስቀሳ ሳይታለል ጊዜውን በጥንቃቄ ማለፍ እንደሚገባ በርካታ አስተያየት ሰጪዎች በኢሳት ላይ እየገለጹ ነው።

ከቀናት በፊት አዳማ ውስጥ ተካሂዶ በነበረው የኦህዴድ ስብሰባ እውቁን የሰብአዊ መብት ተማጋቹን አርቲስት ታማኝ በየነን የሚዘልፉና አማራውን የሚያንቋሽሹ ንግግሮች ሲደረጉ እንደነበር እንዲሁም በኦሮምያ የተነሳውን ተቃውሞ የዘር ጉዳይ አድርጎ ለማቅረብ አመራሮች የማሳመን ስራ ሲሰሩ እንደነበር የኢሳት ታማኝ ምንጮች ገልጸዋል።

በሌላ ዜና ደግሞ በሚዳቀኝና ባለሚ አካባቢዎች ትናንት በበርካታ ቁጥር ያላቸው ወጣቶች፣ እናቶችና ሽማግሌዎች ታፍሰው መታሰራቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት ገልጸዋል።  አንድ የአይን እማኝ የፌደራል ፖሊስ አባላት ልጆችን እንደ ሚዳቆ እያባረሩ እየያዙዋቸው ነው ሲሉ ተናግረዋል