በአምቦ ለደረሰው የሰው እልቂትና የንብረት ውድመት መንግስት ራሱን ነጻ ለማድረግ ዘመቻ ጀመረ

ሚያዚያ ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የአዲስ አበባን አዲሱን ማስተር ፕላን በመቃወም በአምቦና አካባቢው በሚገኙ ከተሞች ወደ አደባባይ የወጡትን ከ40 በላይ ንጹሃን ዜጎች አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ ያስገደለው መንግስት ራሱን ከተጠያቂነት ለማዳን የጀመረውን ፕሮፓጋንዳ በስፍራው ላይ የነበሩ አንዳንድ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ተቃውመውታል።

አፈ ጉባኤ አባ ዱላ ገመዳ በኢቲቪ ቀርበው የተማሪዎችን ጥያቄ ኦነግ እና ግንቦት7 የተባሉት አሸባሪ ቡድኖች አይዟችሁ በማለት አቀጣጥለውታል ብለው ተናግረዋል።

የተማሪዎቹ ጥያቄ ፍትሃዊ ቢሆንም፣ ሌሎች ሃይሎች ግን መጠቀሚያ አድርገውታል በማለት አፈ ጉባኤው አክለዋል።

ጉዳዩን በማስመልከት ጥያቄ ያቀረብንለት የ3ኛ አመት የአምቦ ዩኒቨርስቲ ተማሪ እንደተናገረው አባ ዱላ ገመዳ የተናገሩት ፍጹም ሀሰትና ጨርሶ ያልሆነ ነው ብሎአል።

“በመጀመሪያ ጥያቄውን ለማቅረብ ስንሰበሰብ መልስ እንደሚሰጡን ከነገሩን በሁዋላ ወዲያው በፌደራል እንድንከበብ አደረጉ፣ ትንሽ ቆይተው ፌደራሎች አስለቃሽ ጭስ መተኮስ ጀመሩ። በአካባቢው ቆሞ ሲመለከት የነበረው ህዝብ ተማሪዎችን ለምን ትነኩዋቸዋላችሁ ብሎ ከፖሊሶች ጋር መጋጨቱን ተናግሯል።

ሌላ አንዲት ልጃቸው በገፍ የተገደለባቸው እናት በበኩላቸው፣  በብዛት ያለቁት ከ7 አመት እስከ 11 አመት የሆናቸው ምንም የማያውቁ ህጻናት መሆናቸውንና ህጻናቱ ጥይት ለመሸሽ በሚል ወደ ጫካ ሲገቡ ጨካ ውስጥ መገደላቸውን በመግለጽ እነ አባዱላ እርምጃ የተወሰደው ንብረት ስለወደመ ነው የሚለውን አስተያየት አልተቀበሉትም።

የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶችና አለማቀፍ ተቋማት መንግስት በአምቦ እና በተለያዩ የኦሮምያ አካባቢዎች የፈጸመውን ጭፍጨፋ ማውገዛቸው ይታወቃል።

ሂውማን ራይትስ ወች ግድያውን የፈጸሙትም ሆነ ትእዛዙን የሰጡት ባለስልጣናት ከተጠያቂነት እንደማያመልጡ መግለጹ ይታወሳል።