ሚያዚያ ፳፪ (ሃያ ሁለት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በመተማ ገንዳውሃ ከተማ በፌደራል ፖሊሶች የተገደሉት ሰዎች ቁጥር 5 ሲደርስ 4ቱ በጽኑ ቆስለው በጎንደር ሆስፒታል በመታከም ላይ ናቸው።
የወረዳው መስተዳድር ዛሬ ህዝቡን ሰብስቦ ያነጋገረ ሲሆን፣ ህዝቡ ከዚህ በሁዋላ ከመንግስት ጋር አንተባበርም ማለቱን የአካባቢው ሰዎች ተናግረዋል። አንዳንድ የድርጀቱ አባላት ሳይቀሩ ራሳቸውን ማግለላቸውን ያነጋገርናቸው ሰዎች ገልጸዋል።
ውጥረቱ አሁንም እንዳለ ሲሆን ፖሊሶች አመጹን አስነስተዋል የተባሉትን ወጣቶች ይዘው ማሰራቸውም ነዋሪዎች ተናግረዋል
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአቡነ ሃራ ቤተክርስትያን አገልጋይ የሆኑት ቄስ መልካሙ ማስረሻ በጎንደር ማራኪ በሚባለው አካባቢ ከሚታየው ቤት ማፍረስ ጋር ተያይዞ ቤታቸው የሚፈርስባቸውን ሰዎች በመወከል እስከ ክልል መስተዳደር ድረስ በመሄድ አቤቱታ ሲያሰሙ ከቆዩ በሁዋላ ፣ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ተገድለው መገኘታቸውንና ትናንት የቀብራቸው ስነስርአት መፈጸሙ ታውቋል።
ቄስ መልካሙ ” መንግስት መጀመሪያ ሰዉ ቤት ሲሰራ በንዝህላልነት ዝም ብሎ ስንት እና ስንት ጉልበት እና ገንዘብ ከወጣ በኋላ ይፍረስ ብሎ ማለቱ አላግባብ እና ህዝብን መናቅ ነው” በማለት በተደጋጋሚ ይተቹ ነበር።
በዚህ አቋማቸው የተነሳ ህዝቡ መብቱን እንዲያስከብሩለት ወክሏቸው በተደጋጋሚ ወደ ክልሉ ርዕሰ ከተማ ተጉዘው አቤቱታ አሰምተዋል።
ነገር ግን ከሶስት ቀን በፊት ቤተክርስትያን በአስቸኳይ ትፈለጋለህ ተብሎ ማንነታቸው ባልታወቀ ሰዎች ከተጠሩ በኋላ ተገድለው ተገኝተዋል።
ኢሳት ከአንድ ወር በፊት ቄስ መልካሙን አነጋግሮቸው ነበር። በጊዜው መንግስት ጉዳዩን በጽሞና እንዲያየው ተማጽኖ አቅርበው ነበር። ለትውስታ ይሆን ዘንድ ቄስ መልካሙ በጊዜው የሰጡትን አጭር ቃለምልልስ እነሆ
ይህ በእንዲህ እንዳለ በጎንደር አዘዞ አካባቢ ጋብ ብሎ የነበረው ቤት የማፍረሱ እርምጃ ዛሬ ተጀምሯል። የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት የህዝቡ ወኪሎች ተቃውሞ ለማሰማት ይፈቀድላቸው ዘንድ ዛሬ ወደ መስተዳደር በሚሄዱበት ጊዜ ተይዘው ታስረዋል።