በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች የሚደረገው የተማሪዎች ተቃውሞ እንደቀጠለ ነው

ሚያዚያ ፳፪ (ሃያ ሁለት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከአዲስ አበባ  ካርታ ጋር በተያያዘ የኦሮሞ ተማሪዎች የሚያሰሙት ተቃውሞ በድሬዳዋና  አዳማ ዩኒቨርስቲዎች የቀጠለ ሲሆን፣ በአምቦ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትም ግጭቱ መቀጠሉንና በርካታ ተማሪዎች መታሰራቸው ታውቋል።

በድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ እንዲፈቀድላቸው ቢጠይቁም፣ በግቢያቸውን ውስጥ ተቃውሞ ለማድረግ ተገደዋል። ይህንን ተከትሎ ዩኒቨርስቲውን የወረረው የፌደራል ፖሊስ በርካታ ተማረዎችን ደብድቦ ብዙዎችን ደግሞ ወደ እስር ቤት ልኳቸዋል።

በአዳማ ዩኒቨርስቲም እንዲሁ ተማሳሳይ ተቃውሞ እየተካሄደ ነው። ከኦህዴድ ታማኝ ምንጮች ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው ከትናንት በስቲያ ምክር ቤቱ እስከ እኩለ ሌሊት ባደረገው ስብሰባ በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ተማሪዎችን መስለው የሚገቡ የደህንነት ሰዎች ተመልምለው መረጃዎችን እንዲሰበስቡና እንቅስቃሴውን እንዲቆጣጠሩ ውሳኔ አሳልፏል።

የፌደራል ፖሊሶች በቀጥታ የሃይል እርምጃ የሚወስዱት ተቃውሞው ከዩኒቨርስቲ ግቢ ወጥቶ ህዝቡን እንዳይጨምር በመስጋት መሆኑን ምንጮች አክለው ተናግረዋል።