በጸሃፊዎችና ጋዜጠኞች ላይ የተወሰደው እርምጃ  በቀጣዩ ምርጫ  ላይ ተጽአኖ ለማሳደር ነው ሲል አንድነት ገለጸ

ሚያዚያ ፳፪ (ሃያ ሁለት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ፓርቲው ባወጣው መግለጫ ”  በግል ተነሳሽነታቸው ለሀገራቸው አስተዋፅኦ ለማድረግ ወስነው በብዕራቸው የሰብኣዊ መብት እንዲከበርና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲረጋገጥ በሚወተውቱ የነበሩ የዞን ዘጠኝ አባላትና ጋዜጠኞች ላይ የወሰደው የእስር ርምጃ የሚያመለክተው በቀጣዩ አመት የሚካሄደውን ምርጫ አስመልክቶ የተወሰደ የማሸማቀቅና የወጣቶችን ጥያቄ ለመቀልበስ የሚፈልገው የአምባገነኑ ስርዓት ተግባር ነው” መሆኑን ነው ብሎአል፡፡

ፓርቲው ጸሃፊዎቹና ጋዜጠኞች “በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት የሚሸረሽር ቢሆንም፣  አፈናው ግን ሌሎችን በሺዎች የሚቆጠሩ ብሎገሮችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን ይፈጥራል ብሎአል።

አንድነት “የኢህአዴግ መንግስት የከፈተው የእስር ርምጃ በአስቸኳይ እንዲያቆምና የታሰሩትም ታሰሩ ከተባለበት ሰዓትና ደቂቃ ጀምሮ የሚገኙበትን አጠቃላይ ሁኔታ እንዲጣራ፤ መንግስት ያሰረበትን ተጨባጭ ማስረጃ ካለ ለህዝብ ይፋ እንዲያደርግ፤ ያ ካልሆነ ግን እስረኞቹን በአስቸኳይ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲለቅ” ጠይቋል።

አንድነት ፓርቲ በመጪው እሁድ ሚያዚያ 26 በአዲስ አበባ የተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ ህዝቡን በመቀስቀስ ላይ ይገኛል።  የእሪታ ቀን በሚል በሚጠራው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ በርካታ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጥያቄዎች የሚቀርቡበት ይሆናል። ሰልፉ ቀበና ከሚገኘው የፓርቲው ጽህፈት ቤት ተነስቶ ጃን ሜዳ ላይ ይጠናቀቃል።