ግብረሰዶማዊያንን የሚመለከተው አንቀጽ ወጥቶ የይቅርታ አሰጣጡን የሚያሻሽለውን ረቂቅ አዋጅ አጸደቀ

ሚያዚያ ፳፪ (ሃያ ሁለት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በሥራ ላይ የነበረውን የይቅርታ አሰጣጥና አፈጻጸም ሥነሥርዓት የሚያሻሽለው ረቂቅ አዋጅ ይቅርታ ከማያሰጡ ወንጀሎች መካከል የግብረሰዶም ጉዳይ አንዱ አድርጎ ቢያቀርብም፣ በአቶ አስመላሽ ወ/ስላሴ የሚመራው የፓርላማው የህግ ፣ፍትህና አስተዳዳር ጉዳዮች ቋሚ ኮምቴ የግብረሰዶማዊያን ጉዳይ ከዝርዝሩ እንዲወጣ በማድረግ ሕጉን ትላንት እንዲጸድቅ አደርጓል፡፡

በፍትህ ሚኒስቴር ተረቅቆ በሚኒስትሮች ምክርቤት ጸድቆ፤  በ99 በመቶ በኢህአዴግ አባላት ለተያዘው ፓርላማ መጋቢት 2 ቀን 2006 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ለውይይት የቀረበው ይህው ረቂቅ አዋጅ ይቅርታ የማያሰጡ የወንጀል ጥፋቶችን በዝርዝር ያቀረበ ሲሆን ከነዚህ ድርጊቶች መካከል ግብረሰዶም አንዱ ሆኖ በረቂቁ ተካትቶ ነበር፡፡

ነገር ግን ረቂቅ ሕጉ ለዝርዝር ዕይታ ለቋሚ ኮምቴው ከተመራ በኃላ ኮምቴው የተለያ ወገኖችን አወያይቼ አገኘሁት ባለው መሰረት ይቅርታ የማያሰጡ በሚል የተዘረዘሩትን 12 ገደማ ወንጀሎች እንዲሰረዙና በምትኩም ሌላ አንቀጽ እንዲካተት አድርጓል፡፡ በዚሁ መሰረት “በሌሎች ሕጎች የተደነገጉ ክልከላዎች እንደተጠበቁ ሆነው በዚህ አዋጅ አንቀጽ 3 የተቀመጠውን ኣላማ ለማሳካት ቦርዱ በዚህ አዋጅ መሰረት የሚቀርቡለትን የይቅርታ ማመልከቻዎች ከመንግስትና ከሕዝብ ጥቅም አንጻር በማመዛዘን ያስተናግዳል” በሚል አዲስ አንቀጽ እንዲተካ ተደርጓል፡:

የአንቀጹ በዚህ መልክ መሻሻል በምክርቤቱ የተቃዋሚ ፓርቲ ብቸኛ ተመራጭ የሆኑትን አቶ ግርማ ሰይፋን አስቆጥቷል፡፡ አቶ ግርማ ይህ አንቀጽ ከዝርዝሩ እንዲወጣ የተደረገው በውጪ ኃይሎች ተጽዕኖ መሆኑን በመግለጽ ኢህአዴግ ለተጽዕኖው መበርከኩን አስረድተዋል፡፡ የግብረሰዶማዊያን ጉዳይ ከሕግ ብቻ ሳይሆን ከሕዝብ ሞራል አንጻር ታይቶ ቀደም ሲል በቀረበበት መልክ ይቅርታ ከማያሰጡ ወንጀሎች ዝርዝር ውስጥ እንዲገባ አሳስበዋል፡፡
አንዳንድ የመ/ቤቱ አባላትም ግብረሰዶምን ጨምሮ ሌሎችም እንደሙስና፣ ሽብርተኝነትና የመሳሰሉት ወንጀሎች ይቅርታ ከማያሰጡ ዝርዝር ውስጥ የወጡት ይቅርታ የማያሰጡ ወንጀሎችን ዘርዝሮ መጨረስ ስለማይቻል ነው የሚል መከራከሪያን አቅርበዋል፡፡

ፓርላማው አዋጁን በአብላጫ ደምጽ ትላንት ማክሰኞ ሚያዚያ 21 ቀን 2006 ዓ.ም አጽድቆታል፡፡
የመንግስት ኮምኒኬሽን ሚኒስትር የሆኑት አቶ ሬድዋን ሁሴን በቅርቡ በአዲስአበባ ሊካሄድ ታስቦ የነበረውን የጸረ ግብረሰዶማዊያን ሰልፍን መሰረዙን አስመልክቶ ለኤ.አፍ.ፒ በሰጡት መግለጫ ለፓርላማ የቀረበው የይቅርታ አሰጣጥ አፈጻጸም ሥነሥርዓት ረቂቅ አዋጅ ውስጥ ግብረሰዶምን ይቅርታ ከማያሰጡ ሕጎች አንዱ አድርጎ የሚደነግገውን እንዲሻሻል መደረጉን በመግለጽ በአሁኑ ሰዓት የተቃውሞ አጀንዳ አለመኖሩን መጥቀሳቸው ይታወሳል፡፡

ይህ የሚኒስትሩ መግለጫ ፓርላማው ረቂቅ አዋጁን ከማጽደቁ አስቀድሞ የተሰጠ መሆኑ ፓርላማው አሻንጉሊት መሆኑን በሚገባ የሚያሳይ መሆኑን በሌላ በኩል መንግስት የኒዎሊብራል ኃይሎች እያለ የሚያወግዛቸው እንደዩናይትድ ስቴትአሜሪካ ያሉ
መንግስታትን ድጋፍ ለማግኘት ጉዳዩን ተጠቅሞበታል የሚል ወቀሳን አስከትሎበታል ሲል የአዲስ አበባዋ ዘጋቢያችን ገልጻለች።