ህዳር ፲፰(አስራ ስምንት )ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የሶማሌ ክልል 8ኛውን የብሄር ብሄረሰቦች ቀን ታከብራለች መባሉን ተከትሎ የክልሉን ዋና መቀመጫ ጅጅጋን አርቲስቶች እና የመንግስት ባለስልጣናት በየጊዜው እየጎበኙዋት ነው።
ለበዓሉ ዝግጅት የተመደበለትን 31 ሚልዩን ብር ከዝግጅቱ በፊት ቀድሞ ያጠናቀቀው የሶማሌ ክልል መንግስትን ለበአሉ ማክበሪያ እና ማድመቂያ በማለት ተጨማሪ 14 ሚሊዮን ብር ጠይቋል።
ለበዓሉ ማስተናገጃ የሚሆን ስቴዲየም በመገንባት ላይ የተጠመደው ክልሉ ፤ በገጠመው የበጀት እጥረት የተነሳ በጅምር ባለ ስታዲየም በዓሉን ያከናውናል፡፡ የፌድሬሺን ምክር ቤት ባካሄደው ግምገማ ከ10 ሚልየን ብር በላይ ገንዘብ ያለ አግባብ የባከነ መሆኑን አረጋግጦዋል፡፡ በተመደበው በጀት ዘወትር ከስራ ስዓት ውጭ የከስዓት ጊዜን በመጠቀም የክልሉ ባለስልጣናት ገንዘቡን ጫት ቅመውበታል ሲል ምክር ቤቱ ትችት አቅርቧል።
የፌዴሬሺን ምክር ቤት በበኩሉ የተለያዩ ባለስልጣናትና አርቲስቶች የሶማሌ ክልልን ለማስጎብኝት በሁዱበት ወቅት ለመጓጓዝያ እና ለመስተንግዶ 200 ሚልየን ብር ወጭ አውጥቻለሁ ብሏል፡፡
በዓሉን ለማድመቅ እና የመንግስት ባለስልጣናትን ለማስደሰት በማሰብ በ 243 ሺ ብር ወጭ በጅጅጋ ከተማ ለመለስ ዜናዊ ተብሎ የተቀረፀው ሃውልት እንዲፈርስ ተደርጓል፡፡ በፊደራል አመራሮች ቁጣን የቀሰቀሰው ይህ ምስል ፈጽሞ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ምስል ጋር የማይመሳሰል እና ፈጽሞ በመልክ እና በቁመና የማይገናኝ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ አስተያየት ሰጪዎች ሀውልቱ ከመለስ ይልቅ ግርማ ወልደ ጊዩርጊስን ይመስላል ሲሉ ተሳልቀዋል፡፡ የክልሉ ባለስልጣናት ሃውልቱ የተሸፋፈነበትን ሸራ እንደገለጡ ከፌደራል መንግስቱ ባለስልጣናት በደረሰባቸው ከፍተኛ ትችት ወዲያው በሸራ ሸፍነው አፍርሰውታል። ቀራፂው በቁጥጥር ስር ውሎ ካለፉት ሶስት ሳምንታት ጀምሮ በእስር ላይ ይገኛል፡፡
ለህዳር 29ኙ በአል ከተዘጋጁ ባነሮች መካከል ባቡር ፤ አባይ ግድብ ፤ ቤቶች እና ህገ መንግስት ይገኝበታል። ይህ ባነር ለህዝብ ተደብቆ ከቆየ በኃላ በህዳር 28 ይመረቃል፡፡