ህዳር ፲፰(አስራ ስምንት )ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በኢትዩጵያ የቴሌቪዥን ድራማ ታሪክ በረዥምነቱ ቀዳሚውን ቦታ በመያዝ የሚታውቀው ሰው ለ ሰው ተከታታይ ድራማ 109 ክፍሎች ያህል ከተላለፈ በኃላ፣ ሰዎች በማህበራዊ ድህረ ገጾች የድራማው ተዋንያን የሆነውን በትወና ስሙ አስናቀ የተባለውን ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ባለቤት ከወ/ሮ አዜብ መስፍን ጋር በማመሳስል ገጸባህሪውና ወ/ሮ አዜብ መስፍን ባለስልጣናትን በገንዘብ ይገዛሉ ፤ ፍትህን ይረግጣሉ ፤ በሰው ህይዎት ይነግዳሉ፡ ፤ ሰው ያስገድላሉ፤ ህዝብን ያስለቅሳሉ ፤ በወንጀል ይነግዳሉ፤ ሰው በላ እና ነፍሰ ገዳይ አምባገነን ናቸው ሲሉ እንደሚተቹዋቸው ይታወቃል፡፡
ጉዳዩ ያሳሰባቸው ወ/ሮ አዜብ መስፍን ድራማው የመንግሰትን ስራ እያንቋሸሸ ፤ ከመንግስት ፍላጎት ውጭ እየሄደ በመሆኑ እንዲቀየር የኢቲቪን አስተዳዳሪዎች ማዘዛቸውን የወስጥ ምንጮች ገልጸዋል።
ውስጥ አዋቂዎች ድራማው የወ/ሮ አዜብ መስፍንን ታሪክ የተከተለ እና አብዛኛውን የመንግስት ባለስልጣናት የመክበሪያ ዘዴ የጠቆመ በመሆኑ መንግሰት እንደ ነገሪ ሰሪ ተመልከቶታል ብለዋል፡፡
ጉዳዩ ዙሪያ የኢቲቪን ባለስልጣናት ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።