በሳውድ አረቢያ ምድር የእናቶችና የህጻናት ለቅሶ ቀጥሎአል።

ህዳር ፲፯(አስ ሰባት )ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :-ዛሬ ከሪያድ ወደ አዲስ አበባ ትሄዳላችሁ ተብለው በመኪኖች የተሳፈሩ ኢትዮጵያውያን እናቶችና ህጻናት በድንገት ጉዞዓቸው መሰረዙን ተከትሎ፣ በርካታ እናቶችና ህጻናት ለከፍተኛ የውሀ ጥም በመዳረጋቸው ህይወታቸው አደጋ ላይ ነው።

እናቶች እና ህጻናት ተስፋ በቆረጠ ስሜት ያለቅሳሉ፤ ማለቃችን ነው ድረሱልን ሲሉ ይማጸናሉ። ህጻናቱና እናቶች አስፋልት ላይ ተበትነው በውሀ ጥም ማለቃቸው እንደሆነ ይናገራሉ። ኢሳት በቀጥታ ከስደተኞች ጋር በመገናኘት ሁኔታውን ተከታትሎአል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ አለማቀፍ የስደተኞች ድርጅት ፣ አይ ኦ ኤም፣ እስካሁን 21 ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን ከሳውድ አረቢያ ወደ አገራቸው እንዲገቡ መደገፉን ገልጿል።

በእየቀኑ 12 አውሮፕላኖች ስደተኞችን እያመላለሰ መሆኑን የገለጸው ድርጅቱ፣ ለተመላሾች የአንድ ሌሊት መግብ፣ ውሀና መጠለያ እንዲሁም አገራቸው እስከሚደርሱ የሚሆናቸው የኪስ ገንዘብ መስጠቱን ገልጿል።

በሳውድ አረቢያ ምን ያክል ስደተኛ ኢትዮጵያውያን እንደሚገኙ እንደማይታወቅ የገለጸው አይ ኦ ኤም፣ በሚቀጥሉት ወራት በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ሳውድ አረቢያን ሊለቁ ይችላሉ ብሎአል።

30 ሺ የሚሆኑ ተመላሾችን ለመርዳት 4 ሚሊዮን 5 መቶ ሺ ዶላር እንደሚያስፈልገው የገለጸው ድርጅቱ፣ የተጠቀሰው ገንዘብ በቂ ላይሆን እንደሚችልም አስጠንቅቋል።

አረብ ኒውስ ዛሬ እንደዘገበው ደግሞ የሳውዲ መንግስት ለተመላሽ ስደተኞች ወጪያቸውን እየሸፈነ ነው። በሚቀጥሉት ቀናት 32 ሺ ኢትዮጵያውያንን ለመመለስ እቅድ መኖሩን የሳውዲን ባለስልጣን በመጥቀስ ጋዜጣው ዘግቧል። ተጨማሪ 50 ሺ ኢትዮጵያውያንም በተከታታይ እንደሚመልሱ ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ መንግስት ለስደተኞች እያደረገው ያለው ድጋፍ ሊታወቅ አልቻለም። የተመላሽ ስደተኞችን ወጪ አይ ኦ ኤምና የሳውዲ መንግስት የሚሸፍኑት ከሆነ የኢትዮጵያ መንግስት ድርሻ ከሰዎች ጋር ፎቶ ግራፍ መነሳት ነውን? ሲሉ አንዳንዶች አስተያየት እየሰጡ ነው። በኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ የሚሰራ አንድ ግለሰብ ስደተኞችን እያመጣ የሚያስረክበው አይ ኦ ኤም ሲሆን ከስደተኞች ጋር ፎቶ የሚነሳው ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒሰትሩና ሌሎች የኢትዮጵያ ባለስልጣኖች ናቸው ብሎአል።