ጳጉሜ ፩(አንድ)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የግንባሩ ልሳን የሆነው አዲስ ራእይ እንደገለጸው በህገወጥ መንገድ የሚፈልሱ ሰዎች የመንግስትን ፕሮግራሞች የማይደግፉ ሀይሎችን በመቀላቀል፣ ከጸረ ህዝቦች ጎን እንዲሰለፉ እየተደረጉ በመሆኑ አደጋ ደንቅረዋል።
ልሳኑ ” የዜጎች በህገወጥ መንገድ መፍለስ ለፖለቲካ ፍጆታ በር እንደሚከፍት መታሰብ ያለበት ጉዳይ ነው” ካለ በሁዋላ ” በአሁኑ ወቅት በአገራችን እየተገነባ ያለው የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ መልካም አስተዳደርና ከድህነት ለመውጣት እያደረግን አለነው ትግል የማይጥማቸውና የሚያጣጥሉ ሀይሎች የዜጎቻችንን መፍለስ በተለያዩ ብዙሀን መገናኛ የተለያዩ አፍራሽ ምክንያቶችን በመስጠት እያናፈሱ መሆኑ በግልጽ የሚታወቅ ነው። ስለሆነም በህገ ወጥ መንገድ የወጡ ዜጎች መብት መጣስና ደህንነት መጎዳት ጎን ለጎን ለጸረ ህዝብ ተግባር እንዲሰለፉ እየተረጉ መሆኑን አጽንኦት መስጥትና መከላከል ይገባል” ብሎአል።
ልሳኑ ከትዳራቸው ተለያይተው ወደ ውጭ የሚፈልሱ ሴቶች ቁጥር ከ90 በመቶ በላይ መድረሱን ገልጾ፣ ይህን የህዝብ ቁጥርን ከማዛባት በተጨማሪ በአገር ላይ ማህበራዊ ቀውስ ያስከትላል ብሎአል።
ዜጎች በድህነትና ስራ አጥነት፣ በህበረተሰቡ የተሳሳተ ግንዛቤ ፣ በአገር ውስጥ ያለውን ስራ እድል በመናቅ እየፈለሱ እንደሚሄዱ ልሳኑ ገልጻል።
ህዝቡን ከማስተማር በተጨማሪ በኬላዎች ላይ የተጠናከረ ቁጥጥር መደረግ እንዳለበትም በመፍትሄነት አስቀምጧል።
በሰሜን ወሎና በአንዳንድ የደቡብ አካባቢዎች ተማሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ምምህራንም በገፍ እየተሰደዱ መሆኑን የሚደርሱን ዘገባዎች ያመለክታሉ።
ብዙዎች እንደሚሉት በአገሪቱ ውስጥ ያለው የተስፋ መቁረጥና የተስፋ እጦት ዜጎች አገራቸውን ጥለው እንዲሰደዱ እያደረጋቸው ነው።
ኢህአዴግ በህገወጥ መንገድ የሚሰደዱ ዜጎች ከተቃዋሚዎች ጎን መሰለፋቸው እንዳሳሰበው ሲገልጽ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።