የጎንደር ህዝብ በአስተዳደሩ መማረሩን ገለጸ

ጳጉሜ ፩(አንድ)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከሳምንት በፊት የቀድሞው የኮምኒኬሽን ሚ/ርና የአሁኑ ጠ/ሚ ሀይለማርያም ደሳለኝ አማካሪ አቶ በረከት ስምኦን በመሩት ስብሰባ ላይ ህዝቡ በአስተዳደሩ መማሩን ገልጿል።

50 በመቶ የጎንደር ከተማ ነዋሪ መኖሪያ ቤት የለውም፣ ያሉት አንድ ተናጋሪ ህዝቡ በችግር እየተጠበሰ ስለልማት ቢያወሩት አይገባውም ብለዋል። ህዝቡ መብቱን ሲጠይቅ ተቃዋሚ ነህ እየተባለ እንደሚዘመትበት እኝሁ ግለሰብ አክለው ተናግረዋል።

አንድ ሌላ ተናጋሪ ደግሞ አመራሮች ሲያጠፉ እንደማይቀጡ ገልጸው፣ አሁን እየተደረገ ያለው ግን አንዱን ያጠፋ የቀበሌ አስተዳዳሪ ወደ ሌላ ማዛወር ነው ብለዋል

በጎንደር ከተማ ከፍተኛ የሆነ ሙስና መኖሩን የተናገሩት እኝሁ ተናጋሪ ፣ ስራዎች የሚሰሩት በአበልዥነት ፣ በጎጠኝነትና በዘር መሆኑን ተናግረዋል ። “መቧደን ይቅር፣ አገር በኔትወርክ አይመራም” በማለት በከተማዋ ያለውን የኔትወርክ አሰራር ችግር ዘርዝረው ተናግረዋል

ሌላ ተናጋሪ በበኩላቸው ችግሩ ያለው ቀበሌ ላይ መሆኑን  ህዝቡ በመግለጽ ላይ መሆኑን ተናግረዋል አንዲት ሴትም እንዲሁ በመንገድ እጦት ነፍሰጡሮች አስፓልት ላይ እንደሚወልዱ ፣ በቀን እንደሚዘረፉ ተናግረዋል

አግባብ ባልሆነ ግብር የሰዎች ህይወት እንደሚጠፋ አንድ ሌላ ነዋሪ በስሜት ተናግረዋል

ህዝቡ ሰላማዊ ሰልፍ እንዳያደርግ በይፋ መታገዱን የተናጉት አንድ ተናጋሪ ፣ አስተዳዳሩ እየወሰደ ያለውን እርምጃ ኮንነዋል

አቶ በረከት ሰሞኑን ወደ ተለያዩ አማራ ክልሎች በመሄድ ከህዝቡ ጋር ተነጋገረው ነበር። በጎንነደር አንዳንድ አካባቢዎች ህዝቡ በስርአቱ መማሩን፣ በተለይም ኢህአዴግ እንደከዳቸው ፊት ለፊት ሲናገሩ እንደነበሩ ለማወቅ ተችሎአል።