አሜሪካና ሩሲያ በሶሪያ ጉዳይ ሳይግባቡ ቀሩ

ጳጉሜ ፩(አንድ)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በሩሲያ በተካሄደው የቡድን 20 አገራት ስብሰባ ላይ የተገኙት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ፣ ከሩሲያው አቻቸው ጋር በሶሪያ ላይ ስለሚወሰደው እርምጃ ቢመክሩን ስምምነት ላይ ሳይደርሱ መቅረታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

ፕሬዚዳንት ፑቲን በሶሪያ  የኬሚካል የጦር መሳሪያ ጥቅም ላይ መዋሉን አገራቸው ብትቀበልም ድርጊቱን የፈጸሙት ተቃዋሚዎች እንጅ የባሽር አላሳድ መንግስት አለመሆኑን ገልጸዋል። ተቃዋሚዎች የአለማቀፉ ማህበረሰብ ጣልቃ እንዲገባ በማሰብ ድርጊቱን መፈጸማቸውን ገልጸዋል።

አሜሪካ በበኩሏ ድርጊቱን የፈጸመው የበሽር አላሳድ መንግስት መሆኑን በመግለጽ ወታደራዊ እርምጃው እንደሚቀጥል አስጠንቅቃለች።

ፕሬዚዳንት ፑቲን አሜሪካ በሶሪያ ላይ ጥቃት የምትፈጽም ከሆነ ግልጽ የሆነ የጦር ወንጀል ነው ብለዋል። የጸጥታው ምክር ቤት አባል አገራት ከሆኑት መካከል ሩሲያና ቻይና በሶሪያ ላይ ወታደራዊ ጥቃት እንዲደረግ አይደግፉም። ፈረንሳይ እና እንግሊዝ በአንጻሩ ለአሜሪካ ድጋፋቸውን ገልጸዋል። የእንግሊዝ ፓርላማ አገሪቱ ከአሜሪካ ጎን በመሰለፍ በሶሪያ ላይ ወታደራዊ ጥቃት እንዳትሰነዝር መወሰኑ ይታወቃል።