ነሃሴ ፳፪(ሃያ ሁለት)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ሰንደቅ እንደዘገበው በመጪው እሁድ ነሐሴ 26 ቀን 2005 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ መስቀል አደባባይ የተጠራው ሰላማዊ ሰልፍ በማወዛገብ ላይ ነው።
ቀደም ሲል ሰማያዊ ፓርቲ በዕለቱ ሰልፍ እንደሚያካሂድ ቢያስታውቅም፤ የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጽ/ቤት በበኩሉ ነሐሴ 20 ቀን 2005 ዓ.ም በጽ/ቤቱ በሰጠው መግለጫ በተመሳሳይ ቀን ሰላማዊ ሰልፍ መጥራቱን ይፋ አድርጓል።
ይህንን ተከትሎ በፓርቲው እና የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ “የቀደምኩት እኔ ነኝ” በማለት በመወዛገብ ላይ ሲሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰላማዊ ሰልፍና የስብሰባ ማሳወቂያ ጽ/ቤት በበኩሉ፤ ሰልፍ እንደሚካሄድ ቀድመው ያሳወቁት የሃይማኖት ተቋማቱ በመሆኑ በዕለቱ የሰማያዊ ፓርቲ ሰልፍ የሚካሄድ ከሆነ ህገወጥ ነው ብሏል።
ስለጉዳዩ ተጠየቁት የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት ፤ ፓርቲው ከወር በፊት ነሐሴ 26 ቀን 2005 ዓ.ም ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚያካሂድ በጽ/ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ ማድረጉን በማስታወስ፤ ፓርቲያቸው ሰላማዊ ሰልፉን ለማካሄድ በቅድሚያ ጥያቄ ማቅረቡን ተናግረዋል።
እንደ ሊቀመንበሩ ገለፃ ፓርቲው አስቀድሞ ቀን መቁረጡንና በተባለውም ቀን ሰልፉን ለማካሄድ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰላማዊ ሰልፍ፣ ስብሰባና የማኀበራት ፈቃድ ጽ/ቤት በአካል በመቅረብ ጭምር የማሳወቂያ ደብዳቤ ማስገባቱን ተናግረዋል።
በወቅቱ ጽ/ቤቱ ደብዳቤውን ለመቀበል ፍላጎት ባያሳይም በህጉ መሠረት ማሳወቅ ብቻ በቂ በመሆኑ ደብዳቤውን በጽ/ቤቱ አስቀምጠው መመለሳቸውንና በኋላም ጽ/ቤቱ በፖስታ ቤት በኩል በሬኮማንዴ ለፓርቲው ሰልፍ የት እንደሚያካሂድ፣ ምን ያህል ሰው እንደሚሳተፍ ማብራሪያ በመጠየቁ ፓርቲው በበኩሉ ለጽ/ቤቱ ወዲያውኑ ምላሽ መስጠቱን ተናግረዋል።
ሆኖም ጽ/ቤቱ በህጉ መሠረት በ48 ሰዓታት ውስጥ ምላሽ መስጠት ሲገባው ዝምታን በመምረጡ፣ ዝምታው ደግሞ ሰልፉ እንደተፈቀደ የሚጠቁም በመሆኑ በሰልፉ ዙሪያ ፓርቲው ዝግጅት ማድረግ መቀጠሉን አስታውቀዋል።
ከጽ/ቤቱ እስካሁን ደረስ ምላሽ ባለመገኘቱም ፓርቲው በዕለቱ የጠራውን ሰለማዊ ሰልፍ ከማካሄድ ወደኋላ የሚመልሰው የህግ መሠረት ባለመኖሩ ሰልፉን እንደሚያካሂድ አስታውቀዋል።
ፓርቲው ከነገ ሐሙስ ጀምሮ በአምስት ተሽከርካሪዎች በአስሩም ክፍለ ከተማ መጠነ ሰፊ ቅስቀሳ ለማካሄድ መዘጋጀቱን የተናገሩት ሊቀመንበሩ፤ በመላ ከተማዋና በአካባቢዋም በመቶ ሺህ የሚቆጠር ወረቀት እንደሚበተንና ሰልፉም ካለፈው ሰልፍ ልምድ በማግኘት ከፍተኛ ስራ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለፈው ሰኞ ነሐሴ 20 ቀን 2005 በዋና ጽ/ቤቱ ሰላማዊ ሰልፍ መጥራቱን ያስታወቀው የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የቦርድ ሰብሳቢ ርዕሰ ደብር በሪሁን አርአያ ፤ በዕለቱ ሰማያዊ ፓርቲ ሰላማዊ ሰልፍ መጥራቱን እንደማያውቁና ጽ/ቤታቸውም ቀደም ብሎ ለሰልፉ ሲዘጋጅ መቆየቱን ተናግረዋል።
ርዕሰ ደብር በሪሁን አርአያ የሃይማኖት ጽ/ቤቱ በመስቀል አደባባይ ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ ያሳወቀበትን ቀን ለመናገር አልፈለጉም።
ከዚህም በላይ ሰንደቅ እንዳለው፤ የርዕሰ ደብር በሪሁን መግለጫ የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጽ/ቤት ሰልፉን ለማካሄድ ጥያቄ ያቀረበው ከነሐሴ 15 እና 16 በኋላ መሆኑን የሚያመለክት ነው። በአንፃሩ ሰማያዊ ፓርቲ የማሳወቂያ ደብዳቤ፡ያስገባው ግን ነሐሴ 16 ቀን 2005 ዓ/ም ነው።
ሀቁ ይህ ቢሆንም፤የአዲስ አበባ ሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ ማሳወቂያ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ማርቆስ ብዙነህ፦” የእውቅና ጥያቄ በማቅረብ ቀዳሚ የነበሩት የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጽ/ቤት በመሆናቸው ሰማያዊ ፓርቲ በዕለቱ ሰልፍ እንዲያካሂድ አልተፈቀደለትም” ብለዋል።
አክለውም፦”ፓርቲው ሰልፍ የሚያካሄድ ከሆነም ህገወጥ ነው” ብለዋል።
ሁለቱም ወገኖች የሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ስላሳወቁበትን ቀን እና ስለ ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮች ግን ከመናገር ተቆጥበዋል።