በሀይማኖት ጉዳይ የመጣው ችግር ጊዜ የሚሰጥ አልሆነም ሲሉ አቶ በረከት ተናገሩ

ነሃሴ ፳፪(ሃያ ሁለት)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የጠቅላይ ሚ/ሩ አማካሪ አቶ በረከት ስምኦን ይህን የተናገሩት በመካሄድ ላይ ባለው የሀይማኖቶች ጉባኤ ላይ ነው።

በጉባኤው ላይ የተገኙት አንዳንድ የሀይማኖት አባቶች መንግስት “ትእግስቱን አብዝቶታል፣ እርምጃ ይውሰድልን” እያሉ መጠየቃቸውን ተከትሎ፣ አቶ በረከት ” መንግስት ሀይሉ እንዳለውና መታገሱ ጠቃሚ መሆኑን” ተናግረዋል።  “ይሁን እንጅ” ይላሉ አቶ በረከት “የተፈጠረው ችግር ጊዜ የሚሰጥ አልሆነም”።

አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ ትናንት ባደረጉት ንግግር መንግስት እየወሰደ ያለውን የሀይል እርምጃ እንደሚቀጥል ተናግረው ነበር። በተለይም በአገር ውስጥ ያሉ ተቃዋሚዎች አክራሪነትንና ሽብረተኝነትን መደገፋቸውን ካላቆሙ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው አቶ ሀይለማርያም ገልጸዋል።

በከፍተኛ ውጥረት ውስጥ የሚገኘው መንግስት የፕሮፓጋንዳ ዘመቻውን ከልማት ወደ ሀይማኖት ማዞሩን ዘጋቢያችን ገልጿል።