ነሃሴ ፲፭(አስራ አምስት)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ኢሳት የወረዳው ምንጮች እንደገለጹት ከተባረሩት ሰራተኞች መካከል 2 አቃቢ ህጎች፣ 2 ዳኞች ፣ 1 ፍርድ ቤት ሬስጅስትራርና አንድ ፖሊስ ይገኙበታል። 8 ሰዎች ደግሞ ከስራ ገበታቸው ላይ ለቅቀው ወደ ሌሎች አካባቢዎች ተሰደዋል። የሚታሰሩ ሰዎች እየተበራከቱ መምጣቱን የሚናገሩት ምንጮች፣ 16 ሰዎች ሰሞኑን ተይዘው ታስረዋል።
ካለፈው ወር ጀምሮ በቁጥጥር ስር የዋሉት 40 ሰዎች ደግሞ በዛሬው እለት ወላይታ ሶዶ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ቀርበው ቃላቸውን የሰጡ ሲሆን ፣ ለነሀሴ 22 የጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቶአቸው ወደ እስር ቤት ተመልሰዋል።
የወረዳው ችግር እየተባባሰ መምጣቱ ወደ ግጭት ሊያመራ ይችላል በሚል ሰጉ 60 ወረዳው ሽማግሌዎች ለፌደራል መንግስት አቤት ለማለት በዛሬው እለት ወደ አዲስ አበባ ተጉዘዋል። ባለፉት ወራት ወደ ፌደራል መንግስቱ በመሄድ አቤቱታቸውን ካቀረቡት አገር ሽማግሌዎች መካከል የተወሰኑት ተይዘው መታሰራቸው ይታወቃል። ታዋቂው ባለሀብትና አገር ሽማግሌ ሆኑት መቶ አለቃ ማሴቦ ማዳልጮ፣ ከሶስት ቀናት በፊት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን መዘገባችን ይታወሳል።
ከቀበሌ ቀበሌ መረጃዎችን ያስተላልፋሉ ተብለው የተጠረጠሩ 160 ባጃጅ መኪኖችም እስካሁን ከእስር አልተለቀቁም።
ወደ አዲስ አበባ የተጋዙት የአገር ሽማግሌዎች መንግስት ሰራተኞችንና ማፈናቀል፣ ነዋሪዎች ማሰሩን ካላቆመ፣ የወረዳው ህዝብ የራሱን እርምጃ የሚወስድ መሆኑንና በሚፈጠረው ችግር መንግስት ሀላፊነት የሚወስድ መሆኑን ለማሳወቅ ማቀዳቸውን ከምንጮች ለመረዳት ተችሎአል።
አንድነት ፓርቲ ”መንግስት የመብትና ማንነት ጥያቄ ስላነሱ ያሰራቸውን በአስቸኳይ እንዲፈታ፤ ቁጫዎች ያነሷቸውን ጥያቄዎች አግባብ ባለው መንገድ በፍጥነት እንዲመልስ” መጠየቁ ይታወቃል።
በጉዳዩ ዙሪያ የመንግስት ባለስልጣናትን ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።