በቡሬ ግንባር በሰራዊቱ የሚደፈሩ ሴቶች ቁጥር ጨምሯል

ነሃሴ ፲፭(አስራ አምስት)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በቡሬ ግንባር የሰፈረው የመከላከያ ሰራዊት አባላት በተለያዩ ጊዜያት የአፋር ሴቶችን አስገድደው እንደሚደፍሩ ከስፍራው ደረሰን መረጃ አመለከተ።

የሰራዊቱ አባላት ለቅኝት ወይም ለተለያዩ ስራዎች በሚወጡበት ጊዜ ግመል እና ፍየል የሚጠብቁ ሴቶች ሲያገኙ በሀይል ይድፍራሉ።

ነሀሴ 3 ቀን 2005 ዓም አንዳባ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ሀሊማ አህመድ የሱፍ የተባለች እድሜዋ ከ45 እስከ 50 የሚጠጋ ሴት በሰራዊቱ አባላት ከተደፈረች በሁዋላ ተገድላ በማግስቱ ተገኝታለች። ዳፋሪዎቹ ወታደሮች ስትጠብቃቸው የነበሩትን 20 ፍየሎች መውሰዳቸውም ታውቋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት የመከላከያ ሰራዊቱ እንስሶችን ከመዝረፍ አልፎ ሴቶቻቸውን በሀይል እየደፈሩ መሆናቸው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአፋር ተወላጆች ላይ የመንግስት ታጣቂዎች እያደረሱ ያለው ስቃይ እየተጠናከረ መምጣቱን የሚያመለክት ነው።

በጉዳዩ ዙሪያ የቡሬን ግንባር አዛዦች ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።