በኢትዮጵያ የሚታየው የመብራት መጥፋት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ነዋሪዎች ይናገራሉ

ነሃሴ ፲፭(አስራ አምስት)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ሰሞኑን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ለሳምንታት መብራት የተቋረጠባቸውን አካባቢዎች በማስመልከት ዘገባውን ያጠናከረው ዘጋቢያችን እንደሚለው በየጊዜው እየሄደ ሳይታሰብ የሚመጣው የኤሌክትሪክ ሀይል፣ መንግስት ላለፉት 21 ዓመታት ገነባሁት የሚላቸው የሀይል ማመንጫዎች የት እንደደረሱ ጥያቄ የሚፈጥር ነው።

ያለምንም መብራት መቋረጥ አንድ ሳምንት መድፈን ብርቅ ነው የሚለው ዘጋቢያችን፣ በተለይ የህክምና መስጫ ተቋማት ከመብራት መጥፋት ጋር ተያይዞ በሚፈጠር ችግር በአገልግሎት አሰጣጣቸው ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እየፈጠረ ነው።

የተለያዩ የኢንዱስትሪ ባለንብረቶች ስራቸውን እስከማቆም መድረሳቸውን የስሚንቶ ፋብሪካዎችን በዋቢነት በመጥቀስ ዘግቧል።

በበጋ ውሀ እጥረት አለ በሚል ሰበብ መብራት ይጠፋል፣ በክረምት ደግሞ የማስተላለፊያ መስመሮች ጉዳት ይደረስባቸዋል በሚል ሰበብ መብራት ይጠፋል፣ በየትኛው ወር መብራት እንደማይጠፋ ለማወቅ አልቻልንም ሲል አንድ የግል ኮሌጅ  ተማሪ ገልጿል።

ኑሮዋን የኮምፒተር ቤት በመክፈት የምትመራ ወጣትም በመብራት መጥፋት የተነሳ ብዙ ጉዳት እንደደረሰባት ገልጻ፣ በአሁኑ ጊዜ የቤት ኪራይ ለመክፈል የማትችልበት ደረጃ ላይ መድረሷን አክላለች።

መንግስት የአገር ውስጥ የሀይል ፍጆታን ሳያሟላ ለጎረቤት አገሮች ሀይል በመሸጥና ለመሸጥም በመደራደር ላይ ነው።