ነሃሴ ፩(አንድ)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በድምጻችን ይሰማ የሙስሊም ኢትዮጵያውያን እንቅስቃሴ ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ የገባው መንግስት ፣ በካድሬዎቹ አማካኝነት ” የአገርህ ባንዲራ ተደፍራለችና ስልፍ ውጣ እያለ” ትናንት ህዝቡን ሲያስፈርም መዋሉን የአይን እማኞች ገልጸዋል። አንዳንድ ካድሬዎች “ጊዮርጊስ አድዋ ድረስ ሄዶ ተዋግቷል፣ አንተም አገር ሊያጠፉ የመጡትን ተነስትህ ተዋጋ”የሚሉ ቅስቀሳዎችን መዋላቸውንም እነዚሁ እማኞች ተናግረዋል።
በእድሜ ለገፉት ደግሞ አሸባሪዎችን ለመቃወም ከወጣችሁ እርዳታ እንሰጣችሁዋላን በማለት በድለላ በዛሬው ሰልፍ ላይ እንዲገኙ አድርገዋል። በሰልፉ ላይም ” ፣ አሸባሪነት እናወግዛለን፣ ተቻችለው የሚኖሩትን ህዝብ የሚነጥሉትን ዋህብያዎችን እናወግዛለን” የሚሉ መፈክሮችን አሰምተዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ መንግስት የባንዲራን ክብር ያዋረደውን ግለሰብ ለፍርድ ያቅርብ ሲል ድምጻችን ይሰማ ባወጣው መግለጫ ጠየቀ።
ሐምሌ 19 ቀን 2005 የተደረገው ዓለም አቀፍ ተቃውሞና በአዲስ አበባው ኑር መስጂድ፣ በክልል ከተሞችና በውጪ አገራት የተቀዳጀው ስኬት ያልተዋጠለት መንግስት በዚያው ምሽት በኢትዮጵያ ቴሌቪዠን ባሰራጨው ‹‹ዘገባ›› በእለቱ ተቃውሞ ሙስሊሞች የኢትዮጵያን ባንዲራ እንዳዋረዱ መግለጹን፣ ቴሊቪዥኑ ለተወሰኑ ሰኮንዶች ባቀረበው ቪዲዮ አንድ ግለሰብ ያረጀ እና የተቀዳደደ ባንዲራ ሲያውለበልብ መታየቱን ገልጿል።
ሕገ መንግስታዊ ጥያቄዎችን ያነሳውንና በሰላማዊ መንገድ እየታገለ ያለውን ሙስሊም ህብረተሰብ ማንበርከክ የተሳነው መንግስት ይሄን መሰል ፕሮፖጋንዳ መንዛቱ ከዚህ ቀደም ሲፈጽም የነበረውን ፕሮፖጋንዳ ለተከታተለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ፈጽሞ የሚገርም አይደለም ያለው ድምጻችን ይሰማ፣ መንግስት ሰላማዊ ትግሉን ለመፈንቀል እንኳን ሙስሊሞችን በጸረ-አገርነት መፈረጅ ይቅርና ሌላም ሊፈጽም እንደሚችል የሚታወቅ ሃቅ ነው፡ ብሎአል።
እኛ ኢትዮጵያውያን ለአገራችን ያለን ፍቅር ከሌሎች ወገኖች ጋር የተሳሰርንበት ጠንካራ ገመድ በመሆኑ በተራ ፕሮፓጋንዳ ሊጠለሽ የሚችል እንዳልሆነ ግልጽ መሆን አለበት ያለው የሙስሊሙ ኮሚቴ፣ ልክ እንደሌሎች ወንድሞቹ ሁሉ ኢትዮጵያዊው ሙስሊምም ለባንዲራውና ለአገሩ ፍቅር ደሙን አፍስሶ፣ አጥንቱንም ከስክሶ መክፈል ያለበትን መስዋእትነት ሲከፍል የቆየ በመሆኑ ትግላችን እስከህይወት መስጠት የደረሰ መስዋእትነት እየከፈልን የምንገኘውም ለአገራችን ካለን ከፍተኛ ፍቅር በመነሳት ነው ብሎአል።
ኮሚቴው ” ንቅናቄያችን አገራዊ እና ኢትዮጵያዊነትን የተላበሰ መሆኑ ምንም ጥያቄ የለውም” ሲል ገልጾ፣ ” ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ስለ አገር ያለን ክብር ከሃይማኖታችን አስተምህሮ የመነጨም ጭምር መሆኑን ሁሉም ከግንዛቤ ሊከተው ይገባል” ብሎአል።
መንግስት ደጋግሞ በሚዲያ በነዛው ፕሮፖጋንዳ የሚታየውና የተቀደደ ባንዲራውን የሚያውለበልበው ግለሰብ በመንግስት ተልእኮ የተሰጠው ቅጥረኛ ነው ሲል አክሏል።
” ይህ ሰርጎ ገብ ግለሰብ ይህንኑ ባንዲራ ማውለብለብ ገና ከመጀመሩ በሰኮንዶች ውስጥ በዙሪያው የነበሩ ግለሰቦች ቢያስቆሙትም፣ ይህንኑ ድራማ ለመቅዳት በአንዋር መስጊድ ዙሪያ ባሉ ፎቆች ላይ ካሜራቸውን ደግነው ሲጠባበቁ የነበሩት የመንግስት የካሜራ ባለሞያዎች ይህችኑ ለሰኮንዶች የተሳካችላቸውን ቀረጻ ህብረተሰቡ ሲከለክለውና ሲያስቆመው የሚያሳየውን ትዕይንት ቆርጠው ‹‹ሕዝቡን የሚወክል ነው›› በማለት ለፕሮፖጋንዳ በስፋት ተጠቅመውበታል ሲል መግለጫው አብራርቷል።
መግለጫው በመጨረሻም ” ባንዲራን የማዋረድ ተግባር እኛ ሙስሊሞች አጥብቀን የምናወግዘው ተግባር ሲሆን ከመሰረታዊው የ‹‹ፍትህ ይከበር!›› ትግላችንም በእጅጉ ያፈነገጠ ነው፤ ይህን ባንዲራ የማዋረድ ተግባር የፈጸመው ግለሰብ ማንም ይሁን ማን ተጠያቂ መሆን እንዳለበት እናምናለን፡፡ ግለሰቡ በግሉ በፈጸመው በዚህ የማዋረድ ተግባር ተገቢውን ቅጣት ማግኘት ያለበት ሲሆን ይህንንም ሀላፊነት ሊወስድ የሚገባው መንግስት ራሱ ነው፡፡ መንግስት የተቀደደ ባንዲራ ሲያውለበልብ ለሰኮንዶች ቀርጾ ያሳየውን ግለሰብ በህግ አስከባሪዎቹ በቁጥጥር ስል ማዋልና በአገሪቱ ህግም ተገቢውን ቅጣት የማሰጠት ግዴታ አለበት ፤ የህዝብን ጥያቄ ከመመለስ ይልቅ መሰል አጀንዳዎችን ተጠቅሞ አንድን ህዝብ በሌላው ላይ ለማነሳሳት መሞከር እጅግ አጥፊ ተግባር መሆኑንም በአጽንኦት ልናሳስብ እንወዳለን” ብሎአል።
በተያያዘ ዜና ባለፈው ቅዳሜ ሐምሌ 26 ቀን የመንግስት ወታደሮች በሙስሊም ዜጎች ላይ ያካሄዱትን የጅምላ ግድያ ኢሕአፓ በጥብቅ አውግዞ ወንጀሉን ያዘዙትና ድርጊቱን የፈጸሙትም ባስቸኳይ ለፍርድ እንዲቀርቡ ጠይቋል።
ኢህአፓ ” በግፍ የታሰሩባቸው የሃይማኖት አባቶች (ኢማሞች) እንዲፈቱላቸውም ጠይቋል።
ፓርቲው ” የሰሞኑ የወያኔ አገዛዝ አረመኔያዊ ድርጊት በጽኑ መወገዝ ያለበት ቢሆንም ድርጊቱን በማውገዝና ተቃውሞን በማሰማት ብቻ የወያኔን አረመኔያዊና ጸረ ሕዝብ ጭፍጨፋ ማስቆም አእንደማይቻል ገልጾ፣ የሕዝብን ስቃይና በደል ለአንዴም ለሁሌም ማስቆም የሚቻለው ሁለገብ በሆነ መንገድ ታግሎ አገዛዙን ከስልጣን ማስወገድ ሲቻል ስለሆነ የአገር ፍቅር የሚሰማው ዜጋ ሁሉ ኃይሉን አስተባብሮ በአረመኔው አገዛዝ ላይ ጥቃት እንዲሰነዝር ” ጥሪ እናቀርባለን ብሎአል።
በሌላ ዜና ደግሞ ነጃሺ ጄስቲስ ካውንስል የተባለ ተቀማጭነቱ አሜሪካ የሆነው ድርጅት ባወጣው መግለጫ፣ መንግስት በምእራብ አገራት ኢምባሲዎች ላይ ጥቃት እንደሚፈጸም አድርጎ በማስጠንቀቅ፣ የሙስሊሙን ጥያቄ ለማፈን የሚጓዝበት መንገድ በዜጎች ላይ ጉዳት የሚያደርስ በመሆኑ ከዚህ ድርጊቱ እንዲቆጠብ እንዲያደርጉ ጠይቋል።