በአዲስአበባ የኢታኖል ድብልቅ ቤንዚን ዋጋ ጨመረ

ነሃሴ ፩(አንድ)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በዓለም ገበያ የነዳጅ ዋጋ ባልጨመረበት ሁኔታ በአዲስ አበባ ብቻ የኢታኖል ቤንዚን ድብልቅ ነዳጅ የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ በ0.16 ሳንቲም ከፍ በማለት በሊትር 18 ብር ከ94 ሳንቲም እንዲሸጥ የንግድ ሚኒስቴር መወሰኑን አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴሩ እንዳመለከተው የዓለም የነዳጅ ዋጋ የመዋዥቅ ሁኔታ ማሳየቱን ተከትሎ ጭማሪ ለማድረግ መገደዱን ይግለጽ እንጂ በዓለም ገበያ በዚህ ወቅት ነዳጅ ዋጋ የተለየ ጭማሪ አለማሳየቱን የዜና ምንጮቻችን ገልጸዋል፡፡

በዚሁ መሠረትም በአዲስ አበባ የኢታኖል ቤንዚል ድብልቅ ነዳጅ የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ በሊትር ትላንትና ይሸጥበት ከነበረበት ብር 18 ብር 78 ሳንቲም ወደ ብር 18 ብር ከ94 ሳንቲም ከፍ እንዲል የተወሰነ ሲሆን የተቀሩት የነዳጅ ምርቶች ማለትም ነጭና ጥቁር ናፍታ፣አብዛኛው ህብረተሰብ ለማገዶ የሚጠቀምበት ኬሮሲን፣ የአውሮፕላን ነዳጅ በሐምሌ ወር በሥራ ላይ የነበረው ዋጋ በያዝነው ነሐሴ ወርም በተመሳሳይ እንዲቀጥል ወስኖአል፡፡

በዓለም ገበያ ላይ የሚኖረውን የነዳጅ ዋጋ ሁኔታ መነሻ በማድረግ እንደ አስፈላጊነቱ ከነሐሴ ወር በኃላም ማስተካከያ ሊደረግ እንደሚችልም ሚኒስቴሩ ገልጾአል፡፡

ሚኒስቴሩ በየወሩ የሚያደርገው የነዳጅ ዋጋ ክለሳ ተከትሎ የትራንስፖርት ክፍያ በከፍተኛ ሁኔታ እየናረ የመጣ ሲሆን ይህም የተለያዩ ሸቀጦች ዋጋ እንዲንር ምክንያት ሲሆን ቆይቷል፡፡ በአዲስአበባ በአሁኑ ወቅት የአንድ ሲኒ ቡና ዋጋ ከ5-9 ብር የሚሸጥበት ዋናው ምክንያት ከነዳጅ ጭማሪ ጋር በቀጥታ የተያያዘ ሲሆን የነዳጅ ዋጋ በሚቀንስበት ወቅትም የጨመሩት የሸቀጥ ዋጋዎች ባሉበት መቀጠላቸው የሚታወቅ መሆኑን ዘጋቢያችን ከአዲስአበባ የላከው ዜና ጠቁሟል