የህዳሴውን ግድብ ግንባታ በኢትዮጵያ ሕዝብ መዋጮ ብቻ መሸፈን ወይም ዳር ማድረስ አይቻልም ተባለ

ሰኔ ፫ (ሦስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በሥራ ዓለምም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና በቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ጊዜያዊ ጽሕፈት ቤት በተለያዩ ኃላፊነቶች የሠሩትና የፈረንሳይ አምባሳደር ሆነው ያገለገሉት  አምባሳደር ሀይሉ ወልደጊዮርጊስ  ይህን የገለጹት እሁድ ለህትመት ከበቃው ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር በ ዓባይ ግድብ ዙሪያ  ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ነው።

 

“ የ ዓባይ ውሀ በህግ ላይ የሚያቀርበው ፈተና” በሚል ርዕስ በፈረንሳይኛ  መጽሐፍ ያሳተሙት አምባሳደር ሀይሉ ለህዳሴው ግድብ እስካሁን ከህዝብ የተሰበሰበው ገንዘብ ገና ከ 5 ቢሊዮን ብር እንዳላለፈ አመልክተዋል።

የግድቡ ግንባታ የሚጠይቀው ከ80 ቢሊዮን ብር በላይ ነው  ያሉት አምባሳደር ሀይሉ፤ይህን ያህል ገንዘብ በራሳችን ለማዋጣት ያዳግተናል ብለዋል።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ  የ ዓባይን ግድብ ያለምንም የውጪ እርዳታ በራሳችን እንሠራዋለን በማለት በተደጋጋሚ መናገራቸው ይታወሳል።

 

ያለ እርዳታ ግድቡ የማይቻል መሀኑን ያብራሩት አምባሳደሩ፤ ግብፅ የኤክስፐርቶች ቡድን ያቀረበውን ሪፖርት ተቀብያለሁ ብላ ካረጋገጠች፣ ኢትዮጵያ የውጭ ዕርዳታ ታገኛለች የሚል አመለካከትና እምነት ስላላት ነው >>ብለዋል።

 

አምባሳደሩ አክለውም፦<<ግድቡ ተጠናቅቆ ሥራ ላይ ቢውል ግን ተጠቃሚዋ ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን ግብፅና ሱዳንም የጥቅሙ ተጋሪ ይሆናሉ ።እነሱ ግን ይህ በጎ ጐኑ አይታያቸውም፡፡ የግብፆች ትልቁ ጥርጣሬያቸው ኢትዮጵያ በሕዝቡ መዋጮ ብቻ የግድቡን ግንባታ የማጠናቀቅ ወይም ዳር የማድረስ አቅም ስለሌላት ይህንን ክፍተት ለመሸፈን ከሌሎች አገሮች በስውር ዕርዳታና ብድር ልታገኝ ትችላለች የሚል ነው>>ብለዋል-።

ስለሆነም ይህንን ለማጨናገፍ ሲሉ የማስፈራራት ዘመቻ እያካሄዱ እንደሆነ እና ለዚህም ተግባራዊነት መልዕክተኞቻቸውን ወደተለያዩ አገሮች በመላክ የማግባባት ሥራ እያካሄዱ ስለመሆናቸው የገለጹት አምባሳደር ሀይሌ፤<< ደቡብ ሱዳን እንኳን የትብብር ማዕቀፍ ስምምነቱን እንዳትቀበል ወይም እንዳትፈርም ብዙ ተፅዕኖ አድርገውባት ነበር፡፡ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጐንም እንዲሁ አግባብተዋል፡፡ >>

ከ አምባሳደሩ ገለፃ ለመረዳት እንደተቻለው ከ80 ቢሊዮን ብር በላይ ያስፈልጋል ለሚባለው ለግድቡ ሥራ እስካሁን የተዋጣው ገና 6 በመቶ ያህሉ ነው። ይህ ማለት ከተጀመረ ሁለተኛ ዓመቱን ያስቆጠረው ግድብ ገና 94 በመቶ የሚሆነው ወጭ ይጠብቀዋል። የ ኢትዮጵያ ህዝብ በውድም፣በግዳጅም እንዲያዋጣና ቦንድ እንዲገዛ ተደርጎ የተሰበሰው 6 በመቶ ከሆነ አምባሳደሩ እንዳሉት ግድቡን ያለውጪ ዕርዳታ ካለበት ቦታ ብዙም ማንቀሳቀስ አይቻልም።

ከዚህ አኳያ የግድቡ ሥራ መቀጠልና አለመቀጠል የሚወሰነው ኢትዮጵያ እርዳታን ለማግኘት፤ግብጽ እርዳታን ለማስከልከል እያደረጉ ባሉት ትግል እንደሆነ የዘርፉ ሙያተኞች ይናገራሉ።