ግንቦት ፳፩ (ሀያ አንድ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ባለፈው እሁድ እንግሊዝ ውስጥ ማንችስተር ከተማ ላይ በተደረገው ዓመታዊ የሩጫ ውድድር፤ ዝነኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ በአስደናቂ ብቃት የዓለምን የ10 ኪሎ ሜትር ክብረወሰን በማሻሻል ማሸነፏ ታወቀ።
እስከ አምስት ኪሎሜትር ድረስ ያለውን ርቀት ከኋላ ሆና ስትሮጥ የነበረችው ጥሩነሽ፣ ከዚህ በኋላ ግን ድንገት አፈትልካ በመውጣት ቀሪውን አምስት ኪሎሜትር ውድድሩን በመምራት ነበር ያጠናቀቀችው። አትሌት ጥሩነሽ ውድድሩን የጨረሰችው 30ደቂቃ ከ49 ሰከንድ በመግባት ሲሆን፤ ይህም ሌላዋ ኢትዮጵያዊ አትሌት ብርሃኔ አደሬ ከ7 ዓመት በፊት ካስመዘገበችው የዓለም ክብረወሰን በ18 ሰከንድ የተሻለ ሆኖ ተገኝቷል።
ሦስት የኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት የሆነችው አትሌት ጥሩነሽ፣ ምንም እንኳን በደረሰባት የጤና እክል ምክንያት ባለፈው የለንደን ማራቶን መሳተፍ ባትችልም፣ አሁን ግን በመልካም ጤንነት ላይ እንደምትገኝና በቅርቡም ሞስኮ ላይ በሚደረገው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ የመካፈል እቅድ እንዳላት ገልፃለች። ከዚህም በተጨማሪ በመጪው ቅዳሜ አሜሪካ ውስጥ “ኢዪጂን” (Eugene) ላይ በሚደረገው የዳይመንድ ሊግ ውድድር በ5ሺህ ሜትር ርቀት ለመወዳደር በዝግጅት ላይ መሆኗ ታውቋል።
በማንችስተር የሩጫ ውድድር 5ጊዜ በማሸነፍ ቀዳሚ የሆነውና በቅርቡ 40ኛ ዓመት የልደት በዓሉን ያከበረው፤ እውቁ ኢትዮጵያዊ አትሌት ኃይሌ ገብረ-ሥላሴ፣ በወንዶቹ የ10ሺህ ሜትር ውድድር 3ኛ ሆኖ ጨርሷል። በዚህ ውድድር
ኡጋንዳዊው ሞሰስ ኪፕሲሮ ርቀቱን በ27፡52 በመፈፀም በአንደኝነት ያጠናቀቀ ሲሆን፤ ኬንያዊው ዊልሰን ደግሞ በኡጋንዳዊው ሯጭ በአንድ ሰከንድ ብቻ ተቀድሞ ሁለተኛ በመሆን ውድድሩን አጠናቅቋል፡፡ ኃይሌ በበኩሉ ርቀቱን በ28፡00 ሦስተኛ ደረጃን ይዞ መጨረሱ ታውቋል።
በተያያዘ ዜና ባለፈው እሁድ በኤደንበርግ የተደረገው የማራቶን ውድድር፣ ኢትዮጵያዊው አትሌት ቶላ ለማ አሸናፊ ሆኗል፡፡ ቶላ ውድድሩን በቀዳሚነት ያጠናቀቀው በ2ሰዓት ከ15ደቂቃ ከ32ሰከንድ በሆነ ጊዜ ነበር። አትሌት ቶላ በዓለም አቀፍ የማራቶን ውድድር ሲካፈል ይህ ሁለተኛ ጊዜው ሲሆን ያስመዘገበው ውጤትም ለወደፊቱ ተስፋ ከሚጣልባቸው ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ተርታ የሚያሰልፈው ሆኖ ተገኝቷል በማለት ቅዱስ ሀብት በላቸው ከአውስትራሊያ ዘግቧል።