የኢትዮጵያ ማአድን ልማት አክሲዮን ማህበር የተቋረጠውን የታንታለም ምርት ለመጀመር ፈቃድ ጠየቀ

ግንቦት ፳፩ (ሀያ አንድ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ሪፖርተር እንደዘገበው የኢትዮጵያ ማዕድን ልማት አክሲዮን ማኅበር ከአንድ ዓመት በፊት ያቋረጠውን የታንታለም ኮንሰንትሬት የማምረት ሒደት ለመቀጠል የፕራይቬታይዜሽንና የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲን ፈቃድ ጠይቋል።

በኦሮሚያ  ጉጂ ዞን ሰባቦሩ ወረዳ ቀንጢጫ በተባለ አካባቢ ከ1982 ዓ.ም. ጀምሮ የታንታለም ኮንሰንትሬት ሲመረት ቢቆይም፣  ጥሬ ምርት ከመላክ እሴት በመጨመር የተለያዩ የታንታለም ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ የተሻለ የውጪ ምንዛሬ ማስገኘት ይቻላል በሚል፣ ከሚያዝያ 2004 ዓ.ም. ጀምሮ የታንታለም ኮንሰንትሬት ማምረት መቋረጡን ጋዜጣው አውስቷል።

“ኩባንያው ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው የማዕድን ሚኒስቴር፣ የኩባንያው የዳይሬክተሮች ቦርድና የፕራይቬታይዜሽንና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ የታንታለም ምርት ተቋርጦ የታንታለም ሽቦ፣ ዱቄት፣ ናጌትና ኖቢያም ፔንቶ ኦክሳይድ የመሳሰሉ የተለያዩ የታንታለም ምርቶችን ማምረት የሚያስችል ፋብሪካ በመገንባት እሴት የተጨመረባቸውን ምርቶች አምርቶ ኤክስፖርት በማድረግ፣ የተሻለ የውጭ ምንዛሪ እንዲያስገባ በተሰጠው መመርያ መሠረት መሆኑ” ተመልክቷል።

“በተጨማሪም በቀንጢጫ የሚመረተው ታንታለም ኮንሰንትሬት በተወሰነ መጠን የዩራኒየም ማዕድን ያለው በመሆኑ አንዳንድ የአውሮፓና የሰሜን አሜሪካ አገሮች የዩራኒየሙን ጨረር በመፍራት ታንታለም ኮንሰንትሬቱን ወደአገራቸው ለማስገባት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምክንያት፣ የኢትዮጵያ ማዕድን ልማት አክሲዮን ማኅበር ለማስገንባት ያቀደው ፋብሪካ የዩራኒየሙን ማዕድን ከታንታለም ኮንሰንትሬት ውስጥ ለይቶ ማስቀረት የሚችል እንደሚሆን ” ታስቦ መሆኑ ተገልጿል።

የተቋረጠውን የታንታለም ምርት ለመቀጠል ይቻል ዘንድ በማዕድን ሚኒስትሯ ወ/ሮ ስንቅነሽ እጅጉ ለሚመራው የዳይሬክተሮች ቦርድ ያቀረበው ጥያቄ ይሁንታ ያገኘ ሲሆን፣ ጥያቄውን ለፕራይቬታይዜሽንና ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ አቅርቦ ምላሽ በመጠባበቅ ላይ እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል፡፡

የታንታለም ምርት ሳይቋረጥ የፋብሪካ ግንባታው ሊካሄድ ይችል እንደነበረ የዘገበው  ጋዜጣው ፣ የታንታለም ምርት በመቋረጡ ኩባንያውን ከፍተኛ ዋጋ አስከፍሎታል ብለዋል፡፡ ኩባንያው በዓመት 215 ቶን ታንታለም ኮንሰንትሬት፣ 120 ሺ ቶን ዶሎማይት፣ 7ሺ 500 ቶን ካኦሊንና 5 ሺ  ቶን ኳርትዝ ማዕድናት የማምረት አቅም አለው፡፡

ኩባንያው በዓመት ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ የሚያገኝ ሲሆን ከገቢው 98 በመቶ የሚሆነውን የሚያገኘው ወደ ውጪ ከሚልከው የታንታለም ኮንሰንትሬት ምርት ነው፡፡

ኢሳት ከሳምንታት በፊት የታንታለም ምርት መቋረጡን ተከትሎ አንዳንድ በሙስና የተዘፈቁ ከፍተኛ የህወሀት  ጀኔራሎች ከአንዳንድ የቻይና ባለሀብቶች ጋር በመመሳጠር የታንታለም አፈር በሶማሊላንድ በኩል ወደ ውጭ በማሻገር ከፍተኛ ገንዘብ እየሰበሰቡ መቆየታቸውን መዘገቡ ይታወሳል።

ከታንታለም ማእድን ማውጣት ስራ ጋር የቅርብ ግንኙነት ያላቸው ሰዎች የአገራችን ሀብት በዚህ መንገድ ሲዘረፍ እያየን ዝም አንልም በማለት መረጃዎችን ሰጥተዋል።