ግንቦት ፲፱(ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:- በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች መፈናቀል ምክንያት የሆነውን የኢትዮጵያ የመሬት ፖሊሲ የሚደግፍ 1.3 ቢሊዮን ዩሮ የሰጠውን የእንግሊዝ መንግሥት ለመክሰስ ጠበቃ መቅጠሩን አንድ ኢትዮጵያዊ አስታወቀ።
ሚስተር “ኦ” በሚል ስያሜ በዋሽንግተን ፖስት ላይ ስሙ የሰፈረው ይህ ኢትዮጵያዊ፤ የብሪታኒያ ዓለም-ዐቀፍ የልማት አገልግሎትን ከቤት ንብረታቸው በተፈናቀሉት አራት ሚሊዮን በሚሆኑት ደሀ ኢትዮጵያውያን ስም እፋረዳለሁ ሲል አስታውቋል።
ለም ከሆነውና የዘሩት ሁሉ ይበቅልበታል፣ በማዕድንም ሀብታም ነው ካለው ከጋምቤላ የተፈናቀሉትን ወገኖች በአብነት ያስቀመጠው ይህ ኢትዮጵያዊ ከዚህ ምድራቸው እንዲፈናቀሉና የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዲደርስባቸው የሚያግዝ የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ ወንጀል ነው በማለት ነው የብሪታኒያን ዓለም-ዐቀፍ የልማት ድርጅትን ለመክሰስ ጠበቃ ይዞ የተነሳው።
የልማት ድርጅቱ ለኢትዮጵያ መንግሥት የሰጠው የ1.3 ቢሊዮን ዩሮ የስታሊን አይነት ዘዴን በመጠቀም የተሞላው ማፈናቀል ለሚፈፀምበት ፕሮግራም መደገፊያ ውሎ ዜጎችቹንና ቤተሰቦቻቸውን ከባህላዊ አኗኗራቸውና ኢኮኖሚያቸው አፈናቅሎ ሜዳ የጣለ ነው ብሏል።
ኢትዮጵያዊው የወከለው የለንደኑ የሕግ ድርጅት ተወካይ ሌይ ደይን ዋቢ ያደረገው ዴይሊ ሜይል ዩኬ ድረ-ገፅ፤ የልማት ድርጅቱ ይህ ተግባር የራሱን የሰው ኃይል አገልግሎት ፖሊሲ የተፃረረ ነው በማለት የእንግሊዝ መንግሥትን የ3 ቢሊዮን ዩሮ እርዳታ አግባብ አለመሆኑን ገልጧል።
ይህን በማድረግም የብሪታኒያ መንግሥት የዓለማችን ጨቋኝና አፋኝ የሆኑ መንግሥታትን እየረዳና በሥልጣን እንዲቆዩም እያደረገ ነው ሲል እርዳታው የሚያስከትለውን ውጤት ገልጧል – በኢትዮጵያዊው የተቀጠረው የእንግሊዝ የጥብቅና ድርጅት።
የብሪታኒያ መንግሥት የግብር ከፋዩ ሕዝብ የሚሰበሰበውን ገንዘብ የዓለማችን ደሀ የሆኑ ሕዝቦች ለሚበድሉና ለሚያጠፏቸው ፕሮግራሞች መርጃ ከማዋል ይልቅ፣ በሚረዷቸውና ወደተሻለ ሕይወት በሚያሸጋግሯቸው ፕሮግራሞች ላይ እንዲውሉ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ብሏል።
ከድረ-ገፅ ያገኘነው መረጃ እንዳመለከተው፤ ጠበቃ ቀጥሮ የእንግሊዝን መንግሥት ለመክሰስ የተዘጋጀው ኢትዮጵያዊ ለደህንነቱ ሲባል ስሙን መግለፅ አልተራገፈም ያለ ሲሆን ማንነቱም እንዳይታወቅ በድረ-ገፅ ላይ ፊቱ እንዳይታይ በቅንብር ደብዝዞ ቀርቧል።