በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ፓርቲ በጠራው ሰልፍ የፓርቲ አባላት ሆኑ ሕዝቡ ሊሳተፍ ይገባል አሉ

ግንቦት  ፲፱(ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:- መኢአድ ደግሞ በዚህ በቀሩት ጥቂት ቀናት በ33 ፓርቲ ተመክሮበት ከተስማማን ቅስቀሳ አድርገን ሕዝቡን በስፋት እናሳትፋለን ብሏል።

ዛሬ ከኢሳት ጋር ቃል የተመላለሱት የ33 ፓርቲዎች የጋራ ኮሚቴ ዋና ፀሐፊ አቶ ግርማ በቀለ በሰልፉ ላይ በጋራ አባላትንም ሆነ ሕዝቡን ለማሳተፍ ለመወሰን ነገ የሥራ አስፈፃሚ አስቸኳይ ስብሰባ ጠርተናል ብለዋል።

ሰልፉ በመንግሥት ላይ ያለውን ተቃውሞ በመግለፅ ለትግሉ አንድ እርምጃ ወደፊት በመሆኑ እንደግፈዋለን ያሉት አቶ ግርማ በቀለ፣ አባል ፓርቲዎችም ግለሰቦችም ቢሳተፉበት መልካም ነው ብለዋል።

ያንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ ሕዝብ ግንኙነት አቶ ዳንኤል ተፈራ በበኩላቸው በሰማያዊው ፓርቲ ቀድሞ ጥሪ ተደርጎ ብንመክርበት ኖሮ መልካም ነበር ካሉ በኋላ፤ ይሁንና ሰልፉን ስለምንደግፈው ሕዝቡም ሆነ ፓርቲ አባላቶች ወጥተው ድጋፋቸውን ሊያሳዩ ይገባል ብለዋል።

እንደፓርቲ አቋም ለመያዝ በሥራ አስፈፃሚ ደረጃ ተሰብስበን መወሰን ይገባናል ያሉት አቶ ዳንኤል፣ ስብሰባውን ሐሙስ ለመጥራት ታስቧል ብለዋል።

የመኢአድ ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ኃይሉ ሻውል ሰልፉ ላይ ሕዝቡ ተሳታፊ እንዲሆን በሀገር ውስጥ የመገናኛ ብዙሃንም ሆነ ወረቀት በመበተን ቅስቀሳ አለመደረጉን ገልጠው የ33ቱ ፓርቲዎች ጉባዔ ተቀምጦበት እንድንሳተፍ ከተወሰነ በቀሩት ቀናት ቅስቀሳ ተደርጎ ለሰልፍ እንወጣለን ብለዋል።