በፀጋው ታደለ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ስለኔ የተናገሩት ከራሳቸው ጋር አነፃጽረውኝ በመሆኑ ክብር ተሰምቶኛል አለ

ኢትዮጵያዊው በፀጋው ታደለ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ስለኔ የተናገሩት ከራሳቸው ጋር አነፃጽረውኝ በመሆኑ ክብር ተሰምቶኛል አለ

ግንቦት  ፲፱(ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:- የሞር ሃውስ የ2013 የኮምፒዩተር ሳይንስ ተመራቂ በፀጋው ታደለ አስቂኝ ስም ያለውና ቀጭኑ ሰው ሲሉ በንግግራቸው የጠቀሱት የሳቸው ሰእምም ለአሜሪካኖች እንግዳ (አስቸጋሪ) በመሆኑና በተማሪነታቸው ጊዜ ቀጭኑ ኦባማ ይባሉ እንደነበር ስላነበብኩ እኔንም ከዚህ ማንነታቸው ጋር እንዳመሳሰሉኝ ስለምቆጥረው ኮርቼበታለሁ ብሏል።

በሞር ሃውስ ኮሌጅ ታሪክ በምረቃ ሥነ-ስርዓት ፕሬዚዳንት ሲገኝ የመጀመሪያው በሆነው በ2013 ምረቃ 3.99 በማግኘት የክብር ጸሀላሚ የሆነው በፀጋው ታደለ ለዛሬ ማንነቴ የሃገር ቤት ጠንካራ የሂሳብ ትምህርትና የእናቴ ጥረት ከፍተኛ ድርሻ አላቸው ብሏል።

በሶማሊያ ጦርነት ወቅት ተዋጊ ጀት አብራሪ በመሆናቸው ጀታቸው ተመትቶ በሶማሊያ ጦር እጅ የወደቁት የበፀጋው አባት ለ8ዓመት ተኩል በእስር የወደቁት ለብቻቸው ታስረው እንደነበር (ከቤተሰቡ መስማቱን) የሚናገረው በፀጋው ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል እናቴ በከፍተኛ ሁኔታ በጥናት ትረዳኝ ነበር ይህም ለትምህርት ልዩ ትኩረት እንድሰጥ አድርጎኛል ብሏል።

ከኢሳት ጋር በተናጠል ቃል የተመላለሰው በፀጋው ታደለ የትውልድ መሠረት የልጅነት ዕድሜ በመሆኑ ከ1ኛ እስከ 4ኛ (6ኛ)ክፍል ካሉ ሕፃናት ጋር ለመስራት ከፍተኛ ፍላጎት (ሕልም) አለኝ ያለ ሲሆን በዚህ ዕድሜ የሚገኙትን ሕፃናት መሠረት ማስያዝ በወደፊት ማንነታቸው ላይ መሠረት መጣል ነው ብሏል።

3.99 ያገኘኸው 0.01ዱን ምን ቀንሶብህ ነው ተብሎ የተጠየቀው በፀጋው በመጀመሪያ ዓመት አንድ የእንግሊዛኛ ኮርስ ኤ ማይነስ በማምጣቴ ነው ሲል ከሳቅ ጋር መልሷል።